
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ክስ የመስማት እና ውሳኔ የመስጠት ተግባር በአዲስ (ልዩ ፍርድ ቤት) ሊከወን እንደሚገባ በሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጮች የሕዝብ ምክር እና ግብዓት ማሰባሰብ ተሳታፊዎች አሳሰቡ።
በመድረኮቹ የክስ ሂደቶች በየትኞቹ ጉዳዮች ትኩረት ይደረግ፣ የትኞቹ አጥፊዎች ክስ ይመስረትባቸው፣ ማን ክስ ይመስርት እንዲኹም የማካካሻ፣ የእውነት እና እርቅ ማፈላለግ ጉዳዮች ላይ ሃሳቦች ተሰብስበዋል ያለው የባለሙያዎች ቡድን ነው።
የቅድመ ረቂቅ ፖሊሲ ሕዝባዊ ምክክሮች እና ግብዓት ማሰባሰብ ሥራዎችን የረቂቅ ፖሊሲ እና የድህረ ረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅት ተግባራትን የማከናወን ሙሉ ኀላፊነት የተሰጠው የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን በኅዳር ወር 2015 ዓ.ም በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር እንዲደራጅ ተደርጓል።
የባለሙያዎች ቡድን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሽግግር ፍትሕ እና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ጥናት እና ምርምር ከሚያደርጉ ምሁራንና ከሰብአዊ መብት ተከላካይ ባለሙያዎች ያካተተ ነው። ቡድኑ ከጥብቅና እና ምክር አገልግሎት ዘርፍ፣ ከሲቪል ማኅበራት፣ ከፖሊሲ እና ሕግ ማርቀቅ ባለሙያዎች የተውጣጡ 13 አባላትን ያካተተ ቡድን ነው።
ቡድኑ ሂደቱን አስመልክቶ ሪፖርት አቅርቧል።
የሸግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች የሕዝብ ምክክር እና ግብዓት ማሰባሰብ ሂደት ሪፖርት ሁለት መሠረታዊ ዓላማዎች እንዳሉት ተገልጿል። የመጀመሪያው ዓላማ በሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች ላይ በክልላዊ እና ሀገር አቀፍ መድረኮች እንዲኹም በጽሑፍ የተሰበሰቡ ግብዓቶችን በማደራጀት እና በመተንተን ለሚዘጋጀው የሽግግር ፍትሕ ሀገራዊ ፖሊሲ ይዘት ግብዓት ሊኾኑ በሚችሉበት አግባብ መሰነድ ነው ተብሏል።
ሁለተኛው ዓላማ በፖሊሲ አማራጮቹ ላይ የተገኙ ዋና ዋና ግኝቶች ማጠቃለያዎችን እና ምክረ ሀሳቦችን ዝርዝር ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ነው። የሂደቱ ባለቤት የኾኑት የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ መንግሥት፣ ባለድርሻ አካላት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባላት ሙሉ መረጃ እንዲኖራቸው ያስችላል። በዚህም የሂደቱን ግልጽነት ተዓማኒነት እና ተቀባይነት ለማረጋገጥ ዓላማ ያለው ነው ብለዋል የቡድኑ አባላት።
የባለሙያዎች ቡድን የምክክር እና ግብዓት ማሰባሰብ ሥራውን በይፋ ከጀመረበት ከየካቲት 27 /2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መሰከረም 30/2016 ዓ.ም ድረስ ክልሎች እና ሁለቱ የከተማ መሥተዳድሮችን ያሳተፈ ክልላዊ እና ሀገር አቀፍ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮችን አካሂዷል ተብሏል።
በተለያዩ መርኾዎች ላይ ተመስርቶ በተደረገው ምክክር ግብዓት መሰብሰቡን እና ግኝቶች መኖራቸው ተመላክቷል። ከግኝቶቹ መካከል ከወንጀል ተጠያቂነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፦
👉 በየትኞቹ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የክስ ሂደት ሊኖር ይገባል?
👉በየትኞቹ አጥፊዎች ላይ ክስ ይመስረት?
👉የፍርድ ሂደት ማን ያከናውነው?
👉 የወንጀል ምርመራ እና ክስ የመመስረት ሂደትን ማን ያከናውነው?
👉ዕውነት ማፈላለግ እና እርቅን የተመለከቱ ጉዳዮች፣ የእርቅ፣ የምሕረት እና የማካካሻ ጉዳዮችን ጨምሮ ሌሎችም ተካትተውበታል።
በየትኞቹ አጥፊዎች ላይ ክስ ሊመሰረት ይገባል? የሚለውን የፖሊሲ ጥያቄ አስመልክቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአብዛኛውን ተሳታፊ ድጋፍ ያገኘው ሀሳብ “ከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ባላቸው አጥፊዎች ላይ ያተኮረ የክስ ሂደት ሊኖር ይገባል” የሚለው ነው ብለዋል አባላቱ። በሌላ በኩል ውስን ተሳታፊዎች ሁሉም አጥፊዎች እንደየተሳትፎ ደረጃቸው ተጠያቂ ሊኾኑ ይገባል ብለዋል።
የፍርድ ሂደትን ማን ያከናውነው? በሚለው አብዛኞቹ ተሳታፊዎች “አዲስ ወይም ልዩ ፍርድ ቤት በማቋቋም ክስ የመስማት እና ውሳኔ የመስጠት ተግባር ማከናወን ይገባል” የሚለውን ሃሳብ ደግፈዋል። ውስን ተሳታፊዎች ደግሞ በፌዴራል ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ውስጥ ልዩ ችሎት በማቋቋም ብቁ የኾኑ እና ልምድ ያላቸው ዳኞችን በመመደብ፣ ነጻ እና ገለልተኛ ኾነው እንዲሠሩ በማድረግ ተጠያቂነት ማሰፈን ይገባል ብለዋል።
አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች ደግሞ ክሶቹ መታየት ያለባቸው አዲስ እና ገለልተኛ በኾነ ቅይጥ (የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ባለሙያዎችን ያካተተ) ፍርድ ቤት ወይም በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት አማካኝነት መኾን አለበት የሚል አዲስ አማራጭ አቅርበዋል።
የወንጀል ምርመራ እና ክስ የመመሰረት ሂደትን ማን ያከናውነው? በሚለው ጥያቄ አብዛኞቹ ተሳታፊዎች አሁን ካለው የምርመራ እና የዐቃቤ ሕግ ተቋም ውጭ የምርመራ እና የክስ ሂደቶችን የሚያስተባብር ልዩ፣ ነጻ እና ገለልተኛ የምርመራ እና የክስ ሥራ የሚሠራ ተቋም በማቋቋም ሊከናወን ይገባል ነው ያሉት። የተሻለ ዕውቀት እና ልምድ ያላቸውን የምርመራ ባለሙያዎች እና ዐቃቤ ሕግ በመመደብ ሥራው መከናወን አለበት የሚል አቋም ይዘዋል፡፡
ውስን ተሳታፊዎች ደግሞ አሁን ባለው የፖሊስ እና የዐቃቤ ሕግ ተቋም ውስጥ ተገቢ ልየታ በማድረግ እና የተለየ ቡድን በመመሰረት መሥራት ያስፈልጋል ነዉ ያሉት። ሌሎች ጥቂት ተሳታፊዎች ደግሞ ሥራው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሙያዎችን ባካተተ ወይም በዓለም አቀፍ ተቋም አማካኝነት ሊከናወን ይገባል ማለታቸው ተገልጿል።
ዝርዝር ሪፖርቱና ሂደቱ በፍትሕ ሚኒስቴር ድረ ገጽ እና ሌሎች አማራጮች በፍጥነት ይለቀቃሉ ተብሏል።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!