
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዳማ ከተማ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራ ጥሩ ተሞክሮና ልምድ የቀሰሙበት መኾኑን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ገለጹ።
በዶክተር አሕመዲን ሙሐመድ የተመራ የአማራ ክልል የከተማ ልማት ዘርፍ አመራር አባላት የአዳማ ከተማ ‘ስማርት ከተማ’ ፕሮጀክት ትግበራን ጨምሮ የተለያዩ የዲጂታላይዜሽን አገልግሎት ሥራን በመጎብኘት ላይ ይገኛል።
በጉብኝቱ ከአማራ ክልል ሜትሮፓሊታን ከተሞች፣ መካከለኛና አነስተኛ ከተሞችን ጨምሮ ከ80 ከተሞች የተውጣጡ ከንቲባዎች፣ በየደረጃው ያሉ የዘርፉ መሪዎች፣ የቢሮ ኀላፊዎችና የቋሚ ኮሚቴ መሪዎች ተሳትፈዋል።
ዶክተር አሕመዲን ሙሐመድ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለፁት “የአዳማ ከተማ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራ ትልቅ ልምድ የሚቀሰምበት ነው።” በአዳማ ላይ ጥሩ የለውጥ ሀሳቦች፣ የቴክኖሎጂና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራን ጨምሮ ሌሎች ተግባራት በርካታ ዕውቀትና ልምድ ያገኙበት መኾኑን ገልጸዋል።
”በከተማዋ ዘርፈ ብዙ ውጤት ያየንባቸው ሥራዎች” አሉ ያሉት ዶክተር አሕመዲን፤ በተለይም የሕዝቡ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችና ቅሬታ የተፈታበት የኦቴሜሽን፣ የዲጂታላይዜሽንና ስማርት ደኅንነት ሥራዎችን ተመልክተናል” ነው ያሉት።
የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን በተለይም የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት፣ የመሬት ሀብት አሥተዳደርና አጠቃቀምን በካደስተርና የዘርፉን አገልግሎት በዲጂታል ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማየት መቻሉንም ዶክተር አሕመዲን ተናግረዋል።
”በአዳማ ከተማ የታየውን ተሞክሮ፣ ውጤትና ኢንሼቲቭ ወስደን በአማራ ክልል በስምንት ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ በምናደርገው እንቅስቃሴ የዛሬው ጉብኝት ይረዳናል” ብለዋል።
ከአመራር አባላቱ ባለፈ በቀጣይ የደሴ፣ የጎንደር፣ የደብረብርሃንና ባሕር ዳርን ጨምሮ የተለያዩ የክልሉ ከተሞች ሙያተኞችም ልምዱን ወስደው ሥራውን በክልሉ ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላቸው አቅም እንደሚፈጠርም ተናግረዋል።
የአዳማ ከተማ ከንቲባ ሃይሉ ጀልዴ በዲጂታላይዜሽን ትግበራው በአሁኑ ወቅት 517 ሺህ ፋይሎችን ከወረቀት ወደ ‘ሶፍት ኮፒ’ መቀየራቸውን ተናግረዋል። ከ117ሺህ በላይ የመሬት ይዞታዎችም ወደ ካዳስተር መግባቱንና የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ምዝገባም መጠናቀቁንም ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ከ20 በላይ ሶፍትዌሮችና ሲስተሞች ለምተው ወደ ሥራ ገብተዋል ያሉት ከንቲባው፤ በዚህም ከ122 በላይ አገልግሎቶች በዲጂታል ዘዴ መስጠት መቻሉን አመልክተዋል።
በተጨማሪም ወንጀልን በመከላከል፣ የትራፊክ ፍሰትን ለመቆጣጠርና ‘ስማርት አዳማ’ን እውን ለማድረግ የ’ስማርት ሴኩሪቲ’ ቴክኖሎጂዎች ከሴክተሮች ጀምሮ በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች በሙሉ ተግባራዊ መደረጉን አመልክተዋል።
በዚህም የከተማዋን ገቢ በእጥፍ ከማሳደግ ባለፈ የሕዝቡን የመልካም አሥተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታን መፍታት እንዲሁም ሕገ ወጥ የመሬት ወረራና የተለያዩ ወንጀሎችን መከላከል መቻሉን ከንቲባው መገለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!