
ደባርቅ: ታኅሳስ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ከእዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ መልእክት የብልጽግና አባል ለኾኑ የሰሜን ጎንደር ዞን የመንግሥት ሠራተኞች ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቋል። የዞኑ የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ አቶ ደማሙ ሐብቴ ሥልጠናው ሃብትን መረዳት እና መፍጠር፣ ገዥ ትርክትን መገንባት፣ የሰላም እሴት ግንባታ እና ሥልጡን ሲቪል ሰርቫንት መገንባት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለተከታታይ አምስት ቀናት መሠጠቱን ተናግረዋል።
በርዕሰ ጉዳዮቹ ላይ በርካታ ሃሳቦች እና ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት እንደተደረገባቸውም ተናግረዋል። አቶ ደማሙ ከሥልጠናው በኋላ የመንግሥት ሠራተኞች ከብልሹ አሠራር ወጥተው ማኅበረሰቡን በቀናነት እና በፍትሐዊነት ማገልገል እንደሚጠበቅባቸውም ነው ያነሱት።
በዞኑ ሁሉም የሥልጠና ማዕከላት በመንግሥት ሠራተኞች የተነሱ ጥያቄዎች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ደማሙ ጥያቄዎችን የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ጠቁመዋል። ጥቃቅን ናቸው ተብለው ችላ የሚባሉ ጥያቄዎች ተደምረው ችግር እየፈጠሩ በመኾናቸው መንግሥት የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንደሚሠራም አመላክተዋል።
የሚነሱ ጥያቄዎችን እና የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመንግሥት ብቻ መስጠት አግባብ አይደለም ያሉት ኀላፊው ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል። ከተሳታፊዎች መካከል የዞኑ ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ሠራተኛ የኾኑት ወይዘሮ ሰፈር ሙላት ሥልጠናው ሀገራዊ ፋይዳ ያለው እና ኀላፊነታቸውን በአግባቡ ተረድተው መፈጸም እንዲችሉ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የዞኑ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሠራተኛ የኾኑት አቶ አዲሱ መልኬ ለተከታታይ አምስት ቀናት የተሰጠው ሥልጠና ረጅም ጊዜ የሚፈልግ መኾኑን አንስተው በሀገሪቱ የሚፈጠረውን የሰላም እጦት ለመፍታት እና ልማትን ለማስቀጠል የመንግሥት ሠራተኛውን ሚና ለመለየት ያስቻለ ስለመኾኑም አንስተዋል።
በክልሉ ግጭት ከመፈጠሩ በፊት ማኅበረሰቡ ያነሳቸው የነበሩ በርካታ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል። በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮች የሚያመጡትን ችግር በመረዳት ማኅበረሰቡን በቀናነት ለማገልገል ዝግጁ መኾናቸውንም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡- አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!