የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲኾኑ ትኩረት ሠጥቶ እንደሚሠራ የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት አስታወቀ።

21

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች በወቅቱ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲኾኑ ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ መኾኑን የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ገልጿል፡፡ የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ወቅታዊ የሥራ አፈጻጸሙን አስመልክቶ መግለጫ ሠጥቷል፡፡

የአማራ ክልል መንገድ ሥራዎች ድርጅት ሥራ አሥኪያጅ መብት አድማስ ድርጅቱ በክልሉ የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ተቋቁሞ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ ድርጅታቸው በመንገድ ግንባታው ዘርፍ ተመራጭ እና ቀዳሚ ድርጅት መኾኑን በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡ ድርጅቱ አሁን ላይ በ11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር 15 ፕሮጀክቶችን ይዞ እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ በመንገድ ግንባታ ዘርፉ ከፍተኛ አበርክቶ እንደለው አብራርተዋል፡፡

በ5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በጀት እየገነቡ ያሉት 78 ኪሎ ሜትር መንገድ በተያዘው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ድርጅቱ ከአሁን ቀደም 580 ኪሎ ሜትር ደረጃውን የጠበቀ የጠጠር መንገድ እና 200 ኪሎ ሜትር በላይ አስፓልት መንገድ ሠርቶ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጉንም አብራርተዋል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ ድርጅቱ ከመንገድ ባሻገር ሆስፒታሎችን እና ትምህርት ቤቶችን በመገንባት በሕንጻው ዘርፍ አሻራውን ማስቀመጡን ነው የተናገሩት፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር በበላይነት የሚያስተዳድረው ይህ ድርጅት 93 ማሽነሪዎችን ለመንገድ ሥራው እንደሚጠቀምም ጠቁመዋል፡፡

ድርጅቱ 11 በሙያቸው የተደራጁ ማኅበራትን በሥራው ላይ እያሳተፈ መኾኑን የገለጹት ሥራ አሥኪያጁ ከ3 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ሥራ ፈላጊዎች ሥራ በመፍጠር ኀላፊነቱን እየተወጣ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ባለ አራት ክፍል ትምህርት ቤት በመገንባት ለባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በማስረከብ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን መወጣቱንም ጠቁመዋል፡፡ እንዲኹም 2 ሚሊዮን ብር በማውጣት የአቅመ ደካሞችን ቤት በመጠገን ማስረከቡንም ጠቁመዋል፡፡

ድርጅቱ በሦስቱ ዓመቱ የሰሜኑ ጦርነት ለኪሳራ ተዳርጎ እንደነበርም አብራርተዋል፡፡ ከገጠመው ኪሳራ ለመውጣት በሠራው ተጨማሪ ሥራ አሁን ላይ ትርፋማ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የተገኘው ለውጥ የድርጅቱ ሠራተኞች ያለትርፍ ሰዓት ክፍያ በመሥራታቸው የተገኘ ነው ብለዋል፡፡ የመንገድ ግንባታ ሥራ ዋናው ዘዋሪ ነዳጅ ነው ያሉት አቶ መብት የነዳጅ ችግር እንዳያጋጥም ብዙ ሲሠራ መቆየቱን ነው ያነሱት፡፡ ድርጅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ወቅት ካጋጠመው ኪሳራ ወጥቶ 100 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል ተብሏል፡፡

ከ318 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማውጣት ማሽኖችን መግዛቱ አቅሙን ከፍ ለማድረግ እና ቀጣይ የሚሠራቸውን ሥራዎች በወቅቱ ለማጠናቀቅ ይረዳዋል ብለዋል፡፡ ድርጅቱ ከክልሉ በተጨማሪ በሌሎች ክልሎችም መንገድ እየገነባ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ በተቋሙ የሚገነቡ መንገዶች ጥራታቸውን እንዲጠብቁ እና በወቅቱ እንዲጠናቀቁ የሚያደርግ አሠራር በመኖሩ የተጀመሩ መንገዶች ጥራታቸውን ጠብቀው ከተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ቀድመው እንዲጠናቀቁ እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

አቶ መብት ማኅበረሰቡ የሚገነቡ መንገዶች የኔ ናቸው ብሎ በመያዝ እና ማሽኖችን በመጠበቅ ኀላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡ የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት በ2002 ዓ.ም በ900 ሚሊዮን ብር ካፒታል በ390 ሠራተኞች እንደተቋቋመ ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝን ጨምሮ 40 በሚኾኑ ዘር አባዥ ድርጅቶች የተባዛ ምርጥ ዘር እየተሰበሰበ ነው” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ
Next articleማኅበረሰቡን በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀታቸውን የሰሜን ጎንደር ዞን የመንግሥት ሠራተኞች ተናገሩ።