“የአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝን ጨምሮ 40 በሚኾኑ ዘር አባዥ ድርጅቶች የተባዛ ምርጥ ዘር እየተሰበሰበ ነው” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

13

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2015/2016 የምርት ዘመን በ12 ሺህ 174 ሄክታር መሬት ላይ የተባዛ የሰብል ምርጥ ዘር ምርት እየተሰበሰበ መኾኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

በቢሮው የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ ምርጥ ዘሩ እየተሰበሰበ ያለው የአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝን ጨምሮ 40 በሚኾኑ ዘር አባዥ ድርጅቶች፣ በግል ባለሃብቶች፣ በዩኒየኖች እና ማኅበራት የተባዛ ነው።

ይህም የክልሉን ዘር አቅርቦት እጥረት እንደሚያቃልል አመልክተው ምርጥ ዘሩ የስንዴ፣ የበቆሎ፣ የጤፍ፣ የብቅል ገብስ እና ሌላም የሰብል ዓይነት እንደሚገኝበት አስረድተዋል።
ከዚህም 312 ሺህ 241 ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ ምርጥ ዘር እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡ ምርጥ ዘሩ ለመስኖ እና ለመጪው የመኸር ወቅት ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ ይውላል ብለዋል።

እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም 36 ሺህ 142 ኩንታል የበቆሎ፣ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የማሽላ እና ሌላች ሰብሎችን የመሰብሰብ ሥራ መከናወኑን አስታውቀዋል። የሚጠበቀው ምርት የክልሉን የምርጥ ዘር አቅርቦት ፍላጎት 10 ነጥብ 4 በመቶ መሸፈን እንደሚያስችል አስረድተዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን የሚገኘው የዕድገት ባንድነት የዘር ብዜት እና ግብይት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ ተስፋዬ በሪሁን ዩኒየኑ በ450 ሄክታር መሬት ላይ ያባዛውን የበቆሎ እና የስንዴ ምርጥ ዘር እየሰበሰበ መኾኑን ተናግረዋል።

አቶ ተስፋዬ እንዳሉት ዩኒየኑ በሥሩ በሚገኙ 19 መሰረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከተባዛው ዘርም 12 ሺህ ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ ምርጥ ዘር የሚጠበቅ ሲኾን ዘሩ እየተሰበሰበ ያለው በኮምባይነር በመታገዝ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ ለበጋ መስኖ ስንዴ የዘር ፍላጎት ከአርሶ አደሮች ለሚቀርብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የስንዴ ዘር ፈጥኖ አበጥሮ ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። እስከመጪው ጥር ወር መጨረሻ ዘሩን ሙሉ በሙሉ ሰብስቦ እና አበጥሮ ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።

በ44 ሄክታር መሬት ያባዙትን “ቢኤች 661” የበቆሎ ዘር ጥራቱን ጠብቀው እየሰበሰቡ መኾኑን የገለጹት ደግሞ በዞኑ ወንበርማ ወረዳ በግል ዘር ማባዛት ሥራ የተሰማሩት አቶ መስፍን አስታጥቄ ናቸው።

የእርሻ ኮንትራት ውል ስምምነት ወስደው በአርሶ አደሮች ማሳ ካባዙት የበቆሎ ዘር የጥራት ደረጃውን የጠበቀ 2 ሺህ 100 ኩንታል አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ አመልክተዋል።
ዘሩን ለመጪው የመኸር ወቅት ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ በማዋል የክልሉን የዘር አቅርቦት እጥረት ለማቃለል አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት ከተባዛው 11 ሺህ 986 ሄክታር መሬት 213 ሺህ 700 ኩንታል ምርጥ ዘር ተሰብስቦ ጥቅም ላይ መዋሉ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም እጦቱ ወጣቶችን ሥራ ፈትተው ለመጤ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እንዲጋለጡ ማድረጉን የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ገለጸ፡፡
Next articleየተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲኾኑ ትኩረት ሠጥቶ እንደሚሠራ የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት አስታወቀ።