
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ በወቅታዊ የሥራ አፈጻጸሞች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል። በ2016 በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ የዕቅድ ኦረንቴሽን ሰጥቶ ሥራ መጀመሩንም ገልጸዋል። በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የጤና ሥራውን እየፈተነው መኾኑን ነው ኀላፊው አጽዕኖት ሰጥተው የገለጹት።
በክልሉ የተፈጠረው ግጭት የደርሶ መልስ ክትባትን እንዲቋረጥ አድርጎታል ያሉት ኀላፊው የሕጻናት ጤና አገልግሎት ክትባት ከ60 በመቶ ያልበለጠ ኾኗል ብለዋል። ከየደረጃው የጤና አመራር ጋር በመወያየትም ለማሻሻል እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የጸረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ለማድረስ የመንገድ መዘጋት ችግር ፈተና መኾኑን ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል። በዚህም 700 የመድኃኒቱ ተጠቃሚ የነበሩ ወገኖች አቋርጠዋል ብለዋል፡፡ ያቋረጡትን መድኃኒት እንዲቀጥሉ ለማድረግ መድኃኒት የማፈላለጉ ሥራ እየተሠራ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
በቲቪ እና በወባ መከላከል ላይም ተመሳሳይ ችግር እየገጠመ እንደኾነ ነው ኀላፊው ያብራሩት። የወባ ሕሙማን ቁጥር መጨመሩንም ተናግረዋል፡፡ የወባ መከላከያ የቤት ውስጥ ኬሚካል ርጭት በ6 ወረዳዎች ብቻ የተከናወነ ሲኾን የሚያስፈልጋቸው 30 ወረዳዎችን ማዳረስ አለመቻሉን ጠቁመዋል። አጎበር በማሰራጨት በኩልም አቅርቦት ስላልተገኘ እስካሁን አለመሰራጨቱን ጠቅሰዋል። ኅብረተሰቡን የመከላከል ዘዴዎች ላይ የማስተማር ተግባሩ መቀጠሉን ግን ተናግረዋል።
እንደ ደም ግፊት እና ስኳር የመሳሰሉ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች እየጨመሩ መኾኑን ኀላፊው ገልጸዋል። እንደ ኀላፊው ማብራሪያ የመድኃኒት አቅርቦትም የመቆራረጥ ችግር እያጋጠመ ነው። የመድኃኒት ተጠቃሚዎችም ተከታትለው መውሰድ ላይ ችግር ስለመኖሩ ነው ያብራሩት።
የኮሌራ በሽታ በ9 ዞኖች የተከሰተ ሲኾን 4 ሺህ 800 ሰዎችን ማጥቃቱም ተነስቷል። ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመመካከር እና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በተሠራ ሥራ በሽታውን መቆጣጠርም ተችሏል። ድርቅ በ9 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 59 ወረዳዎች በመከሰቱ የምግብ እጥረት ማጋጠሙን ኀላፊው ገልጸዋል። ኀላፊው ለዚህም ሰሜን ጎንደር ዞን እና ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደርን ለአብነት ጠቅሰዋል። እንደ ኀላፊው ገለጻ ከ5 ዓመት በታች ዕድሜ ባሉ ሕጻናት ከፍተኛ የምግብ እጥረት ታይቷል።
አጥቢ እና ነፍሰ ጡር እናቶች ላይም ተመሳሳይ ችግር እያጋጠመ መኾኑን ነው ቢሮ ኀላፊው የገለጹት። አልሚ ምግብ እና መድኃኒቶችን ለማቅረብ እየተሠራ ነው፤ ይሁን እንጅ በቂ ስላልኾነ ለጤና ሚኒስቴር ጥያቄ መቅረቡን አብራርተዋል። ከድርቁ ጋር ተያይዞም እየመጡ ያሉ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች የከፉ መኾናቸውን ነው የገለጹት።
በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት 270 የጤና ተቋማት መዘረፋቸውን፤ ታካሚ እና መድኃኒት ማመላለሻ የነበሩ 43 አንቡላንሰ እና 17 ሌሎች መኪናዎች መውደማቸውን ነው ኀላፊው የገለጹት። ይህም ለጤና አገልግሎት አሰጣጡ እንቅፋት እንደኾነው ገልጸዋል። ችግሩን ለመቋቋም የጎደለውን ለማሟላት እየተሞከረ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ኀላፊው የአጋር አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
በክልሉ ውስጥ የጤና ሥራዎችን ተደራሽ ለማድረግ የ341 ፕሮጀክቶች ግንባታ መኖሩን ኀላፊው አሳውቀዋል። ይሁን እና በሥራ ላይ ያሉት 89 ብቻ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። 252 ፕሮጀክቶች ሥራ ላይ አለመኾናቸውን ገልጸው ተቋራጮች እና አማካሪዎችን በማወያየት ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ነው ኀላፊው የተናገሩት።
ኀላፊው የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎትንም አጠናክሮ ለማስቀጠል በአብዛኞቹ ዞኖች የንቅናቄ መድረኮች እየተካሄዱ ነው ብለዋል። ከጥር 1/2016 ዓ.ም ጀምሮም በሁሉም አካባቢ አባል የማፍራት ሥራ ይጀመራል ብለዋል። ያለፉ ጊዜያት ሥራዎችን ከሆስፒታል እና ከዞን የሥራ ኀላፊዎች ጋር በመገምገም የጸጥታ ችግሩ ሳይበግረን መሥራት እንዳለብን ተስማምተናል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!