
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጣና ሐይቅ ላይ የዓሳ ልማትን የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ መሆኑን የባሕር ዳር ዓሳ እና ሌሎች የውኃ ላይ ሕይወት ምርምር ማዕከል አስታወቀ።
የምርምር ማዕከሉ በመጪው ሳምንት ከ200 ሺህ በላይ የዓሳ ጫጩቶችን ለማሰራጨት በዝግጅት ላይ ነው ተብሏል። የምርምር ማዕከሉ ዳይሬክተር እና የማህበራዊ ምጣኔ ሃብት ተመራማሪ አቶ እርቄ አስማር ከኢፕድ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት በጣና ሐይቅ ላይ የሚስተዋለው የሕገ ወጥ ዓሳ አስጋሪዎች እንቅስቃሴ በሐይቁ የዓሣ ሃብት ላይ አሳሳቢ ስጋት ፈጥሯል ብለዋል።
በሐይቁ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና ለመቀነስ በጣና ሐይቅ ላይ የዓሳ ግብርና የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው ተብሏል። አቶ እርቄ የዓሳ ጫጩቶች በሕገ ወጥ መንገድ በአስጋሪዎች ከውኃ አካላት እየወጡ ለገበያ እየቀረቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ይህም የዓሳ ብዝሃ ሕይወት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንዲገኝ አድርጎታል ብለዋል።
የምርምር ማዕከሉ በሐይቁ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ መኾኑን አመልክተው። ማዕከሉ በተለይም የዓሳ ጫጩቶችን በሰው ሠራሽ መንገድ በማስፈልፈል እና በማባዛት ወደ ጣና ሐይቅ ከመጨመር በተጨማሪ ሁሉም በየቤቱ ዓሳ ማስገር እንዲችል በክልሉ የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት በኩል በየደረጃው እየተሰራ ነው ተብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!