
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ለማሳደግ ክልሉ ለአካባቢ እና ለአረንጓዴ ልማት ጥበቃ ሥራዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ገልጿል።
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ለማምጣት የሚያስችል ስትራቴጅ ነድፋ በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች። ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ልማትን ለመገንባት ከተመረጡት ዘርፎች መካከል ግብርና፣ ደን፣ ውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ዘርፎች ቀዳሚዎች ናቸው፡፡
የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኀላፊ ተስፋሁን ዓለምነህ ባለፉት ዓመታት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን መሠረት ያደረጉ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ሲሠራ መቆየቱን አንስተዋል።
የደን ባለቤትነት፣ የአየር ብክለት ቁጥጥር፣ የኢንዱስትሪ በካይ ተረፈ ምርቶች፣ ኬሚካሎች እና ደረቅ ቆሻሻ አያያዝ፣ አጠቃቀም እና አወጋገድ ማሻሻል ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ኀላፊው ገልጸዋል።
አቶ ተስፋሁን በክልሉ የሚገኙ የደን ቦታዎች ልማት እና ጥበቃ የማሳደግ ሥራ ትኩረት የተሠጣቸው ጉዳዮች መኾናቸውንም ጠቁመዋል። በክልሉ የተከሰተው የፀጥታ ችግር የተቀመጡ ተግባራትን በሙሉ አቅም ለመፈጸም እንደ አንድ ችግር ተነስቷል። በቀጣይ በሁሉም አካባቢዎች የደን እና የአካባቢ ጥበቃ እና ልማት ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም ድጋፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!