
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚያገለግል የቆጣሪ ውል እድሳት ማድረግ ጀምሯል።
ከኅዳር 1 እስከ ታኅሣሥ 16/2016 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ 100 ሺህ ደንበኞች ውላቸውን ማደሳቸውንም አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡ ተቋሙ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን በማሰብ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚያገለግል የቆጣሪ ውል እድሳት እያደረገ ይገኛል።
የውል እድሳት ዓላማው ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት እና ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች በቀላሉ ምላሽ መስጠት ነው ተብሏል። የውል እድሳቱ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ቆጣሪዎችን ለማወቅና አዳዲስ ቆጣሪዎችን ለደንበኞች ለመስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር መላኩ ታዬ የውል እድሳቱ ዓላማ ደንበኞችን በሚገባ ማወቅና የደንበኞችን ፍላጎት መሠረት ያደረገ አገልግሎት መስጠት ነው ብለዋል።
ቆጣሪን ለማይታወቅ አካል የሚያስተላልፉ ደንበኞችን ለመቆጣጠርና የኀይል ሥርቆትን ለማስቀረት እንዲሁም የኀይል መቆራረጥ ችግርን ለማቃለል እንደሚያስችል አመልክተዋል።
ደንበኞች እስከ መጋቢት 30/2016 ዓ.ም በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ በተቋሙ ቅርንጫፎች በመገኘት ውላቸውን እንዲያድሱም ነው አቶ መላኩ ያሳሰቡት። ውል ከፈጸሙ አምስት ዓመት የሞላቸው ደንበኞች እንዲያድሱ የሚገደዱ ሲኾን አዲስ የሚያድሱት ውል ደግሞ ለአምስት ዓመት የሚቆይ እንደኾነ አብራርተዋል።
ኢዜአ ያናገራቸ የውል እድሳቱ ተጠቃሚ አቶ ሳሙኤል ነጋሽ፣ ወይዘሮ ሐና ዘሪሁን እና አቶ እንዳለ ክንፈ የውል እድሳት አገልግሎቱን ለማግኘት በሄዱባቸው ቅርንጫፎች ሁሉ ያለ ምንም እንግልት መስተናገዳቸውን ጠቅሰዋል።
የደንበኞች የክፍያ አገልግሎት በባንኮችና በቴሌብር የሚሰጠው በነፃ ቢኾንም አንዳንድ ግለሰቦች በ”ዲጂታል እንክፈልላችሁ” በሚል እያጭበረበሩ እንደሚገኙ ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ደንበኞች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ተቋሙ መልዕክት አስተላልፏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!