
ደብረ ብርሃን: ታኅሳሥ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገራዊ የፍትሕ ማሻሻያውን መነሻ በማድረግም የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ፣ ፖሊስ ኮሚሽን እና የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን በክልሉ ለሦስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ የአገልግሎት ማሻሻያ ሰነድ አዘጋጅተዋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሀኑ ጎሽም እንዳሉት በተለያዩ ጊዜያት የፍትሕ ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ የተሳለጠ ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት የአገልግሎት አሰጣጥ የማሻሻያ ሥራዎች ተሠርተዋል።
ይሁን እንጂ በእነዚያ ማሻሻያዎች በሚፈለገው ደረጃ እርካታ ማግኘት እንዳልተቻለ አስታውቀዋል። በመኾኑም የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን መሠረት በማድረግ የክልሉ ሕዝብ በፍትሕ ተቋማት የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ እና በፍትሕ ተቋማቱ ላይ እምነት እንዲኖረው ቅንጅታዊ አሠራርን ያማከለ ማሻሻያ መደረጉን አብራርተዋል።
የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያው የተቋማትን አሠራር እና አደረጃጀት የሚፈትሽ ሲኾን የሥራ መሪዎች እና ባለሙያዎች የሕዝቡን ርካታ እንዲያሳድጉ ማዘጋጀትም የማሻሻያው ግብ ነው ተብሏል።
የፍትሕ አገልግሎት ማሻሻያውን ወደ መሬት ማውረድ በተጀመረበት ወቅት የጸጥታ ችግር መፈጠሩን ያነሱት ቢሮ ኀላፊው አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው የክልሉ አካባቢዎች ወደ ተግባር ለመግባት ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑ ጠቅሰዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ፍትሕ መምሪያ ኀላፊ ደመረ ቸሬ ለጸጥታ መደፍረስ ችግሩ ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ተጠቃሽ መኾኑን አንስተዋል።
የሕዝቡን የፍትሕ ፍላጎት ለማርካት የማሻሻያ እቅዱን ወደ ተግባር ማውረድ እንደሚገባም አንስተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት ሃሳብ የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ እቅዱ የሕዝቡን ችግር በተጨባጭ መፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል። አሁናዊ የጸጥታ መደፍረስ ችግሮች በማሻሻያ እቅዱ መሠረት በሙሉ አቅም ለመሥራት ፈታኝ ሊኾን እንደሚችልም ተናግረዋል። መንግሥት አስፈላጊ ምቹ ሁኔታዎችን ሊፈጥር ይገባል የሚል ሃሳብ ከተሳታፊዎች የተነሳ ሲኾን ወደ ተግባር ለመግባትም ተቋማዊ ቅንጅትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።
የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ከምስራቅ አማራ ቀጣና ከተውጣጡ የፍትሕ ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር በማሻሻያ እቅዱ ላይ ውይይት አድርጓል።
ዘጋቢ፦ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!