
ሰቆጣ: ታኅሳስ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በዝቋላ፣ በስሃላ ሰየምት እና በአበርገሌ ወረዳዎች ብቻ ከ791 ሺህ 596 በላይ እንሰሳት አፋጣኝ የእንሰሳት መኖ እንደሚያስፈልጋቸው የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምህረት መላኩ ተናግረዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ቆላማ አካባቢዎች ማኅበረሰብ አርብቶ አደር በመኾናቸው በርካታ የእንሰሳት ቁጥር የያዙ ናቸው ያሉት ኀላፊው ወደ አጎራባች ወረዳዎችም ከ171 ሺህ በላይ እንሰሳት ግጦሽ ፍለጋ ተሰደዋል ነው ያሉት።
አቶ ምህረት እስከ አሁን በሦስቱ ወረዳዎች ከ10 ሺህ 400 በላይ እንሰሳት መሞታቸውን ገልጸዋል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ሄልቫተስ የተባለ መንግሥታዊ ያልኾነ ድርጅት 2 ሺህ 160 ኩንታል ምጥን መኖ ድጋፍ ማድረጉን ነው ያስረዱት፡፡ አቶ መላኩ የተደረገውን ድጋፍም ለ450 አርሶ አደሮች ማከፋፈል ስለመቻሉም አስገንዝበዋል።
ከችግሩ አሳሳቢነት የተነሳ ቅድሚያ ለሰብዓዊ ድጋፍ ቢጠየቅም በእንሰሳቱ ላይ የደረሰው የመኖ እጥረት ግን የከፋ ነው ብለዋል። መላው ኢትዮጵያውያን የውኃ መያዣ ጋን፣ የእንሰሳት መድኃኒት እና የመኖ ድጋፍ እንዲያደርግም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሕዝብ ስም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!