“የታጣቂዎችን የተሳሳተ ዓላማ በውል በመገንዘብ የክልሉ ሕዝብ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅቶ ዘላቂ ሰላም ማስፈን ይጠበቅበታል” ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ

31

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኮማንድ ፖስቱ ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ አመራሮች እንዲሁም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የጸጥታና የደኅንነት ኃላፊዎች ጋር በመኾን በቀጠናው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት በጎንደር ከተማ አካሂዷል። የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥና የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ በአማራ ክልል ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በሠራዊቱ ስኬታማ የግዳጅ አፈጻጸምና በኀብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ መምጣቱን ተናግረዋል።

ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ በአማራ ክልል የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠልና የሕዝቡን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ የአሥተዳደርና የጸጥታ አካላትን መዋቅር ማጠናከር አስፈላጊ ስለመኾኑ አሳስበዋል። ሁሉም አካላት ኀላፊነታቸውን በቁርጠኝነት እንዲወጡ ማድረግ አሰፈላጊ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጥበብ በተሞላበት የግዳጅ አፈጻጸምና ለሕዝቦች ሰላምና ደኅንነት በከፈለው መስዋዕትነት ክልሉን በማፍረስ የብጥብጥና የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ሲጥሩ የነበሩ አካላትን ህልም ማክሸፍ ችሏል ብለዋል ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ።

የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ዓላማና ተግባር የአማራን ሕዝብ ስቃይ ማራዘም፤ ሕዝቡን ተስፋ ማስቆረጥ፤ የልማት አውታሮችን ማውደምና እንዲዳከሙ ማድረግ ነበር ብለዋል። “የታጣቂዎችን የተሳሳተ ዓላማ በውል በመገንዘብ የክልሉ ሕዝብ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅቶ ዘላቂ ሰላም ማስፈን ይጠበቅበታል” ሲሉም ተናግረዋል።

ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ በአማራ ክልል የዕዙ ክፍሎች ባሉበት ቀጠና ሁሉ ትኩረቱን ከሃይማኖት አባቶች፣ ከምሁራን፣ ከተለያዩ የሕዝብ አደረጃጀቶችና ባለሃብቶች ጋር ያደረገ ውይይት መካሄዱ ለተገኘው አንጻራዊ ላላም የላቀ አስስዋፅኦ እንደነበረው ጠቁመዋል። የተጀመረውን ሕዝባዊ ውይይት ስር ነቀልና ችግር ፈቺ በኾነ መልኩ ማስቀጠል ይገባል፤ የሰላምና የልማት ሥራዎችን አስተሳስሮ መሄድም ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።

ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የውይይቱ ተሳታፊዎች ሕዝቡ ሰላም የሚያደፈረሱ አካላትን ዓላማ እና ድርጊት እየኮነነ ነው ብለዋል። ታጣቂዎችም ቢኾኑ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው መግባት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። በየደረጃው የሚገኝ የመሥተዳድር አካላትና የጸጥታ መዋቅር የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠልና ሕዝቡን ወደ ልማት ለመመለስ ማንኛውንም መስዋዕትነት በመክፈል ኀላፊነትን መወጣት ይጠበቅበታል ሲሉም ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው የመመለስ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የደቡብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ገለጸ፡፡
Next articleከ791 ሺህ በላይ እንሰሳት አፋጣኝ የእንሰሳት መኖ እንደሚያስፈልጋቸው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።