ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው የመመለስ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የደቡብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ገለጸ፡፡

18

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተማሪ ሠርካለም አዳሙ ትባላለች፡፡ በደቡብ ጎንደር ዞን ጉና በጌምድር ወረዳ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ናት። ከ9ኛ ክፍል ወደ 10ኛ ክፍል ደረጃ ይዛ አልፋለች። ትምህርቷን አጠናቅቃ ለራሷ፣ ለሕዝብ እና ለሀገር የሚጠቅም ሥራ ለማከናወን ህልም ሰንቃለች፡፡ ለዚህም ጊዜዋን በአግባቡ ተጠቅማ ታጠናለች፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የትምህርት ሂደቱ መሰናክል በዝቶበታል፡፡ ተማሪ ሰርካለም በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ትምህርቷን አቋርጣለች።

ከመስከረም እስካሁን ድረስ ለ3 ጊዜ መቋረጡን እና በመማር ማስተማሩ ላይ ተጽዕኖ መፈጠሩን የተናገረችው ተማሪ ሠርካለም ”እንኳን ለሦስት ወር አንድ ክፍለ ጊዜ ሲያመልጥ እንኳን ያንገበግባል” ነው ያለችው። ብዙ ትምህርት እንዳመለጣት እና ትምህርት ሲከፈትም ለማካካስ እያሰበች መኾኑን ጠቁማለች። አሁንም ግን ማንበብን መደበኛ ሥራዋ አድርጋዋለች፡፡

የተማሪ ሠርካለም እናት ወይዘሮ ይመኝ ገላው ልጃቸው ትጉህ እና ለትምህርት ትኩረት የምትሰጥ ተማሪ መኾኗን ነግረውናል። ”ምን ያደርጋል! ከዓላማ ልትደናቀፍብኝ፤ ልትከፋብኝ ነው” በማለትም የልጃቸው ሕይወት እንደሚያሳስባቸው ነው የተናገሩት።

”እሷ የምታስበው ትምህርቷን እንጂ የደኅንነቷ ጉዳይ አይደለም፤ እኛ ሕጻን ስለኾነች ደኅንነቷ ያሰጋናል” በማለት የልጃቸው ሕይወት እና ቀጣይ እጣ ፈንታ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል፡፡ እናቷ ዘላቂ ሰላም መጥቶ ልጃቸው ወደ ትምህርት ቤት እንድትሄድ ምኞት እና ጸሎታቸው መኾኑን ነግረውናል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደስታ አስራቴ በሰላም እጦት ምክንያት አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እየሠጡ እንዳልኾነ አንስተዋል፡፡ የዞኑ አሥተዳደር፣ ሕዝቡ እና መከላከያ ሠራዊት በሠሩት ቅንጅታዊ ሥራ የዞኑ ሰላም እየተረጋጋ መኾኑን አቶ ደስታ ጠቁመዋል። ስለኾነም የትምህርት እና የግብርና ልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል እየተሠራ ነው። እንደ አቶ ደሥታ ገለጻ ትምህርት ያቋረጡ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው የመመለስ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለጹት፡፡

ተማሪዎች በግጭቱ ምክንያት የተኩስ ድምጽ እየሰሙ መማር አለመቻላቸው እውነትነት አለው ያሉት ምክትል አሥተዳዳሪው በሰበብ አስባቡ ትምህርት ቤት የሚዘጉ እንዳሉም ጠቁመዋል። የመማር ማስተማር ሥራው ሲቋረጥ የሚጎዱት ተማሪዎች ብሎም የክልሉ ሕዝብ ስለመኾናቸውም ተናግረዋል። ”ትምህርት ቤቶችን በመዝጋት መፍትሄ እንደማይገኝም” ሲሉም ጠቁመዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሰራዊት አዛዥ ጋር ተወያዩ
Next article“የታጣቂዎችን የተሳሳተ ዓላማ በውል በመገንዘብ የክልሉ ሕዝብ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅቶ ዘላቂ ሰላም ማስፈን ይጠበቅበታል” ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ