
ባሕርዳር: ታኅሳሥ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አርሰናል በኤምሬትስ ስታዲየም ከዌስት ሃም የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ኾኗል፡፡ አርሰናል በዚህ ውድድደር ዘመን 18 ጨዋታዎችን አድርጎ 12ቱን አሸንፏል፡፡ በአራት አቻ ወጥቷል፡፡ በሁለቱ ደግሞ ተሸንፎ 40 ነጥብ በመሰብሰብ ከመሪው ሊቨርፑል በሁለት ነጥብ ብቻ አንሶ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በሚኬል አርቴታ የሚሠለጥነው አርሰናል በኤምሬትስ ስታዲየም ያደረጋቸውን ያለፉትን አምስት የፕሪሜየር ሊግ ጨዋታዎች በማሸነፍ ጠንካራ አቋም አሳይቷል ሲል ዴይሊ ሜይል ስፖርት በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
በተጨማሪም አርሰናል ከዌስትሃም ጋር ባደረገው ያለፉት 13 የሊግ ጨዋታዎች 12ቱን መርታት ችሏል፤ይህም የቡድኑን ጠናካራነት ያሳያል ተብሏል። የመድፈኞቹ አሠልጣኝ አርቴታ” በጨዋታው ውጤት በቀላሉ የምናገኝ አይመስለኝም፤ በጣም አስቸጋሪ ጨዋታ ይኾንብናል፡፡
“የተጋጣሚያችን አሠልጣኝ ጥሩ ቡድን የሠሩ ጠንካራ ሰው ናቸው፡፡ ዌስት ሃም በዚህ የውድድር ዘመን ወጥ አቋም እያሳየ ነው፡፡ ስፐርስን እና ማንቸስተር ዩናይትድን ማሸነፉ የቡድኑን ጥንካሬ ይነግረናል፡፡ ስለዚህ ከጨዋታው አስቸጋሪነት አንጻር እኛ ክፍተታቸውን እና ድክመታችንን ለይተን በመስራት በሁሉም ነገር ተዘጋጅተናል፤ እናሸንፋለን! ” ብለዋል፡፡
የአርሰናሉ አማካኝ ካይ ሃቨርትዝ አምስት ቢጫ ካርድ በማየቱ በዛሬው ጨዋታ እንደማይሰለፍም ተነግሯል፡፡ የአርሰናል አሰላለፍም 4-3-3 ይኾናል ሲል ቢቢሲ አስነብቧል፡፡
አርሰናል ዌስት ሃምን ካሸነፈ ነጥቡን 43 በማድረስ ፕሪሜየር ሊጉን ለመምራት ያስችለዋል፡፡
የመድፈኞቹ ተጋጣሚ መዶሻዎች ከ18 የፕሪሜየር ሊግ ጨዋታዎች ዘጠኙን አሸንፈዋል፡፡ በሦስቱ አቻ በመውጣት እና በስድስት ጨዋታዎች ተሸንፈው በ30 ነጥብ ደረጃቸው 7ኛ ነው፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ዌስትሃም ባለፈው ሳምንት ማንቸስተር ዩናይትድን 2-0 በኾነ ውጤት አሸንፏል።ካለፉት ሰባት የሊግ ጨዋታዎች አምስቱን ማሸነፍ የቻለ ቡድንም ነው፡፡ ይህም የዴቪድ ሞይስ ቡድን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ይጠቁማል፡፡ አሰልጣኝ ዴቪድ ሞይስ በጨዋታው ዙሪያ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
“አርሰናል ከባድ ቡድን ነው፤ ቡድኑ ካለው ወቅታዊ አቋም አኳያ የሚጫወተው ለማሸነፍ ነው፤ እኛም ለማሸነፍ ስለምመንጫወት ጨዋታው ወሳኝ ስለመኾኑ ጥያቄ አያስነሳም ::
“ሚኬል አርቴታ ወደ አርሰናል ከገባ ጀምሮ አስገራሚ ውጤት እያመጣ ነው፡፡ የኤፍኤ እና የኮሙኒቲሺልድ ዋንጫን አሸንፏል፡፡ይህ የቡድኑን ጥንካሬ ያሳየናል፡፡ ለማንኛውም እኛ አሸንፈን ከፍ ለማለት ስለተዘጋጀን እናሸንፋለን ” ብሏል፡፡
የዌስት ሃም አሰላለፍ 4-2-3-1 ይኾናል ሲል የቢቢሲ አምደኛ አድሪያን ክላርክ ጽፏል፡፡የዕለቱን ጨዋታ ማይክል ኦሊቨር በዋና ዳኛነት ይመሩታል፡፡ ስቱዋርት ቡርትና ዳን ኩክ በመስመር ዳኝነት ተመድበዋል፡፡ ሮብ ጆንስ አራተኛ ዳኛ ሲኾኑ ክሬግ ፓውሰን እና ኧን ሁሲን ደግሞ ቫሩ ላይ ይሰየማሉ፡፡
በሌላ ብራይተን ከቶትንሀም ሆትስፐር የሚያደርጉት ጨዋታም የዛሬ መርሐ ግብር አካል ነው፡፡ በትናንት ጨዋታዎች ዎልቨስ ብሬንትፎርድን 4ለ1 ፤ቸልሲ ክሪስታል ፓላስን 2ለ1፤ማንቸስተር ሲቲ ኤቨርተንን 3ለ1 አሸንፈዋል፡፡ ፕሪሜየር ሊጉን ሊቨርፑል በ42 ነጥብ ይመራዋል፡፡ አርሰናል በ40 ነጥብ ሁለተኛ እና አሰቶን ቪላ በ39 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ይገኛሉ።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!