አማራ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ጠቅላላ ሃብቱ 28 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገለጸ፡፡

79

አዲስ አበባ: ታኅሳስ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አማራ ባንክ ሁለተኛውን የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው። በጠቅላላ ጉባኤው ባንኩ የ2015 በጀት ዓመት አጠቃላይ አፈፃፀሙን ለባለአክሲዮኖች አቅርቧል።

በሪፖርቱ ባንኩ በበጀት ዓመቱ የቀረቡለትን ዕድሎች በመጠቀም ተልዕኮውን መወጣት እንደቻለ ተነስቷል፡፡ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት መልካም ዕሴቶችን በማቅረብ ንቁ እንቅስቃሴ ያደረገበት እና ከሚጠበቀው በላይ ውጤት ማስመዝገብ የተቻለበት እንደነበርም ተብራርቷል።

በነበረው የሃብት ማሠባሠብ ሥራ እ.ኤ.አ እስከ ሰኔ 30/2023 ድረስ 19 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ማሠባሠብ ተችሏል፡፡ ከተሠበሠበው ውስጥ ለሀገር ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለሚያደርጉ ሴክተሮች ወደ 14 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱም ተገልጿል፡፡

ባንኩ የግብርና ሥርዓትን ለማዘመን ለአርሶ አደሮች በ222 ሚሊዮን ብር ትራክተር ገዝቶ ማቅረብ መቻሉንም የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሠብሣቢ መላኩ ፋንታ ገልጸዋል።
በጉባኤው ባንኩ ከተደራሽነት አንፃር በመላ ሀገሪቱ ያለውን የቅርንጫፍ ቁጥር ከ290 በላይ ማድረስ መቻሉ ተነስቷል።

የቦርድ ሠብሳቢው በአንድ ዓመት ብቻ በዲጂታል ባንኪንግ ዘርፍ ተጨማሪ 125 የኤቲኤም ማሽን አዘጋጅቶ በማቅረብ ለደንበኞቹ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደኾነም ጠቁመዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባንኩ ጠቅላላ ሃብቱ 28 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር እንደኾነ እና የተከፈለ ካፒታሉ 5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መድረሱ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት አዛዥ ጀነራል ሞሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ አዲስ አበባ ገቡ።
Next articleበእንግሊዝ ፕሪሜየር ሊግ ዛሬ አርሰናል ከዌስት ሃም ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡