”ጥያቄዎቻችን የሚመለሱት ተከፋፍለን ስንጋጭ ሳይኾን በአንድነት ስንቆም ነው” የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ

23

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሰላም ለገቡ ወጣቶች የሚሰጠው ሥልጠና ተጀምሯል። የከተማ አሥተዳደሩ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ጌትነት አናጋው የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ሰበብ በማድረግ የግል እና የቡድን ፍላጎታቸውን ለማሣካት የሚፈልጉ ኃይሎች ወደ ግጭት ማምራታቸውን ገልጸዋል። ሰላም በመጥፋቱ የክልሉ ምጣኔ ሃብት ጉዳት ደርሶበታል ሲሉም ተናግረዋል። የውጪ ጠላቶቻችን ባደረጉት ቅስቀሳ ግጭቱ መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።

አቶ ጌትነት ”ጥያቄዎቻችን የሚመለሱት ተከፋፍለን ስንጋጭ ሳይኾን በመነጋገር እና በመግባባት በአንድነት ስንቆም ነው” ብለዋል። ጥያቄዎቻችን አደራጅተን ለሚመለከተው አካል ስናቀርብም መልስ እናገኝላቸዋለን ሲሉም አክለዋል።

ኀላፊው ጦርነት የሕይወት እና የአካል ጉዳት ያስከትላል፤ አምራች የኾነውን የማኅበረሰብ ክፍልም ለአካል ጉዳት ይዳርጋል ነው ያሉት። በሰሜኑ ጦርነት ያጋጠመው ቀውስ እስካሁን እንዳላገገመ አብራርተዋል። ስለኾነም አሁን የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ መመካከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

አሁን ላይ ሥራዎች ቆመው ትኩረቱ ሁሉ ግጭቱ ላይ መኾኑን ኀላፊው ጠቅሰዋል። ይህ ደግሞ ለክልሉ ቀውስ መባባስ እና ለጥያቄዎቹ አለመመለስም ምክንያት እንጅ መፍትሄ አይሆንም ነው ያሉት።

ጥያቄዎቻችን እንዲመለሱልን የሌሎች ክልል ሕዝቦች ሊደግፉን ይገባልም ብለዋል። ለዚህም የክልላችን ሰላም ወሳኝነት አለው፤ በሰላሙም በልማቱም ስንደጋገፍ ተሰሚም ተጽዕኖ ፈጣሪም መኾን እንችላለን ነው ያሉት፡፡

አቶ ጌትነት ለሠልጣኞቹ ”የክልሉ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብላችሁ በመምጣታችሁ አክብሮት አለኝ” ብለዋል፡፡ ሥልጠናውን ወስዳችሁ ወደ ማኅበረሰቡ ትቀላቀላላችሁ ብለዋል።

ከማንኛውም ጫና እና ችግር ይልቅ ለሕዝብ እና ለሀገር ቅድሚያ ሰጥታችሁ አስፈላጊውን መስዋእትነት ሁሉ በመክፈል ኀላፊነታችሁን እንድትወጡ ሲሉም አሳስበዋል።
ሥልጠናው ለ10 ቀናት የሚቆይ መኾኑም ታውቋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሳዑዲ አረቢያ ለኢትዮጵያ ዜጎች የሥራ እድል ስምሪት መስጠቷን እንደምትቀጥል ገለጸች።
Next articleየሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት አዛዥ ጀነራል ሞሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ አዲስ አበባ ገቡ።