ሳዑዲ አረቢያ ለኢትዮጵያ ዜጎች የሥራ እድል ስምሪት መስጠቷን እንደምትቀጥል ገለጸች።

25

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ልዑል አብዱልአዚዝ ቢን ሳዑድ ቢን ናይፍ በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሌንጮ ባቲን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በውይይታቸው ልዑል አብዱልአዚዝ ቢን ሳዑድ ቢን ናይፍ ሳዑዲ አረቢያ ለኢትዮጵያ ዜጎች የሰጠችውን የሥራ ስምሪት ዕድል በሰፊው እንደምትቀጥል ገልጸዋል። ልዑሉ “ሕጋዊ ባልኾነ መንገድ የሀገሪቱን ድንበር ጥሰው የገቡና በማቆያ የሚገኙ ዜጎችን በሚመለከት በጋራ መሥራት ያሥፈልጋል” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለሳኡዲ አረቢያ ታሪካዊ ወዳጅ እና ጥብቅ አጋር መኾኗንም አንስተዋል። በሁለቱ ሀገራት መካከል ስላለው የንግድ፣የትምህርትና ቀጠናዊ ትብብርም ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ሌንጮ ባቲ በሳዑዲ አረቢያና በኢትዮጵያ መካከል እየተሻሻለ የመጣውን የሁለትዮሽ ግንኙነት አድንቀው፤ በቀጣይ ከዜጎች ጉዳይ ባለፈ በሌሎች የትብብር መስኮች በጋራ ለመሥራት በኢትዮጵያ በኩል ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል።

በቀጣይም በሀገራቱ መካከል ሊኖሩ በሚገባቸው የትብብር መስኮች ዙሪያም መምከራቸውን በሪያድ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ ኑ በዓላትን በጋራ እናክብር ” የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ጣሂር ሙሐመድ
Next article”ጥያቄዎቻችን የሚመለሱት ተከፋፍለን ስንጋጭ ሳይኾን በአንድነት ስንቆም ነው” የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ