
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ታላላቅ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ እና ባሕላዊ በዓላት ይከበራሉ፡፡ በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው የሰላም እጦት በርካታ በዓላት ሳይከበሩ ቆይተዋል፡፡ በክልሉ በታላቅ ሥነ ሥርዓት የሚከበሩት ልደትን በላሊበላ እና ጥምቀትን በጎንደር እየደረሱ ነው፡፡ እነዚህን በዓላት በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ለእንግዶችም ጥሪ ቀርቧል፡፡
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ጣሂር ሙሐመድ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የሰሜኑ ጦርነት እና አሁን ላይ በክልሉ ያለው የሰላም እጦት ቱሪዝሙን እየጎዳው መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡
በተለይም አማራ ክልል የተፈጠረው ወቅታዊ የሰላም እጦት ለክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ በክረምት ወቅት የሚከበሩ በርካታ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት መከበር ሳይችሉ መቅረታቸውንም አስታውሰዋል፡፡
የጸጥታ ችግሩ ከተፈጠረ ጀምሮ በክልሉ በመንቀሳቀስ መደበኛ ሥራ ለማከናወን ችግር መግጠሙንም አስታውቀዋል፡፡ የቅርስ እድሳት እና እንክብካቤ፣ የባሕል ማጎልበት፣ የአገልግሎት ዘርፍ እና የመዳረሻ ልማት ሥራዎችን ለመሥራት የሰላም እጦት እንቅፋት እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት ተከትሎ ጎብኝዎች ባለመምጣታቸው መሰረታቸውን ቱሪዝም ላይ ያደረጉ ሆቴሎች፣ አስጎብኝዎች እና ማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ነው ያሉት፡፡ የክልሉ መንግሥትም ከቱሪዝም ማግኘት የሚገባውን ገቢ ሳያገኝ ቀርቷል ነው ያሉት፡፡
የኑሮ መሰረታቸውን በቱሪዝም ብቻ ያደረጉ መኖራቸውን የተናገሩት ኀላፊው የሰላሙን ጉዳይ በፍጥነት አስተካክሎ ወደ ቱሪዝም እንቅስቃሴው መመለስ ካልተቻለ ከዚህ የባሰ ችግር ይገጥማል ነው ያሉት፡፡
የሰላም ተስፋ መምጣት ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ ካልተቻለ በቱሪዝም ዘርፉ ለመሥራት መሻት ብቻ በቂ አለመኾኑንም ነው የተናገሩት፡፡ ቱሪዝም ለሰላም ይሠራል፤ ሰላምም ለቱሪዝም ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ አሁን ያለው የሰላም ተስፋ በቀጣይ ለሚከበሩ በዓላት ትልቅ እድል መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የሰላም ጥሪ መደረጉ ለቱሪዝሙ ዘርፍ ትልቅ ተስፋ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ልደትን በላሊበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር መጥቶ ለማክበር የሚጓጓው ብዙ ነው ያሉት ኃላፊው ለዚህም የሰላም ጥሪው ጠቀሜታው ላቅ ያለ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ቢሮ ኀላፊው ከኮሮና ቫይረስ እና ከሰሜኑ ጦርነት ማግስት በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው ሰላም በቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በ2014 እና በ2015 ዓ.ም ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት በድምቀት መከበራቸውንም ገልጸዋል፡፡ በጦርነት ዳፋ ውስጥ የነበረው አካባቢ በቱሪዝም እንቅስቃሴው ተነቃቅቶ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
ባሕልን ማስተዋወቅ ከገቢ ምንጭነት ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላትን በሰላማዊ መንገድ አክብሮ ለሌሎች መሸጥ የሕዝብን በጎ እሴት ለማስተዋወቅ እና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ለማሳደግም ታላቅ ድርሻ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡
በታኅሳሥ እና በጥር ወራት የሚከበሩ በዓላት በሰላም ሲከበሩ የማይነቃቃ እና የማይንቀሳቀስ ተቋም አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡ በዓላቱ ለኢንቨስትመነት እድል እንደሚፈጥሩም ተናግረዋል፡፡
አቶ ጣሂር ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ የነበረውን የሰላም እጦት ለበዓላት ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መዘግየት ምክንያት መኾኑን ገልጸዋል። አሁን ላይ ልደትን በላሊበላ እና ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ልደትን በላሊበላ ለማክበር ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡ የሥራ ክፍፍል መደረጉንም አንስተዋል፡፡
የበዓሉ ወቅት የመጓጓዣ አሠራር የተሳካ እንዲኾን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ “ኑ ሃይማኖታዎ እና ታሪካዊ በዓላትን በጋራ እናክብር፤ ታሪክን፣ ሃይማኖትን አይታችሁ ትሄዳለችሁ” ሲሉም ቢሮ ኀላፊው ኢትዮጵያውያን ወደቦታው በመምጣት በዓላቱን እንዲታደሙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አቶ ጣሂር በአማራ ክልል ከተነገሩት በላይ ሲያዩዋቸው የሚያስደንቁ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ ስፍራዎች እና በዓላት መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡
“አሁን ላይ በዓላቱን ማክበር በሚያስችል ኹኔታ ላይ ስላለን ሁሉም ወገናችን ወደ አማራ ክልል መጥቶ አብሮን እንዲያከብር እንጋብዛለን” ብለዋል፡፡
ሰላም ሲመጣ ከቱሪዝም የሚጠቀም ሁሉም ነው፣ ሰላም ሲመጣ እኔም እጠቃማለሁ ብሎ መሥራት እና ለሰላም እኔ ኀላፊነት አለብኝ ብሎ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ በጥምረት በመሥራት ሰላሙን ማረጋገጥ ከተቻለ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ወደ ቀድሞው መመለስ ብቻ ሳይኾን የበለጠ ማሳደግ ይቻላል ብለዋል፡፡
አቶ ጣሂር ጎብኝዎች በዓላትን ለማክበር ወደ ክልሉ ሲመጡ በወጉ ተቀብሎ ማስተናገድ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አሳስበዋል፡፡ እንግዶች ሲመጡ የተዘጋጉት እንደሚከፈቱ እና የተዳከመው ምጣኔ ሃብትም እንደሚነቃቃ ነው የተናገሩት፡፡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩም አቶ ጣሂር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!