“ለሁሉም ጉዳይ መሰረት የኾነው ሰላም ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ይገባል” አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

15

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 13 ቋሚ ኮሚቴዎች የሁለት ወር አፈጻጸማቸውን ከአስተባባሪ ኮሚቴ ጋር በመኾን እየገመገሙ ነው። ከሕዝቡ የሚነሱ የኑሮ ውድነት፣ የመልካም አሥተዳደር እና ሌሎች ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ ቅድሚያ ለሠላም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ዋና አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናግረዋል፡

ዋና አፈ ጉባኤው “ለሁሉም ጉዳይ መሰረት የኾነው ሰላም ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ይገባል” ሲሉም አስገንዝበዋል። ለዚህም ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት ተናግረዋል። በተለይም ለዘላቂ ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው የብሔራዊ ምክክር መድረክ ቶሎ ወደ ሥራ እንዲገባ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች በክትትልና ቁጥጥር ሥራቸው እያንዳንዱ ተቋም ሰላምን በሚመለከት ሀገራዊ አስተሳሰብን መገንባት ላይ ምን እየሠራ እንደኾነ መፈተሽ እንደሚገባ መገለጹንም የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በክትትልና ቁጥጥር ሥራ የመጡትን ለውጦች በመገምገም ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲኖር ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ለሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፤ በቀጣይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በአግባቡ መድረሱን ማየት ይገባል ነው ያሉት፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራት የኑሮ ውደነቱን ለመቀነስ የሚያግዙ በመኾናቸው ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራባቸው እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቋሚ ተክልን በመስኖ ለማልማት በትኩረት እየሠሩ መኾኑን በቃብትያ ሁመራ ወረዳ በመስኖ ልማት ላይ የተሠማሩ አርሶ አደሮች ተናገሩ።
Next article“ ኑ በዓላትን በጋራ እናክብር ” የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ጣሂር ሙሐመድ