
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዓመቱን ሙሉ ያለማቋረጥ የሚፈሱ ከ10 በላይ ወንዞች ይገኛሉ።
በርካታ አርሶ አደሮች በጊዜያዊ እና ቋሚ ተክል ምርት ውጤታማ ለመኾን በመስኖ ልማት ሥራ ላይ ተሠማርተዋል። በዞኑ በቃብትያ ሁመራ ወረዳ የማር ውኃ ቀበሌ አርሶ አደሮችም የመስኖ ጥቅምን በመረዳት የቋሚ ተክል ምርትን በስፋት እያመረቱ ነው።
በቃብትያ ሁመራ ወረዳ የማር ውኃ ቀበሌ በቋሚ ተክል ምርት ላይ ተሠማርቶ ያገኘነው ወጣት ይደግ ማለደ 200 የማንጎ ተክሎችን በመንከባከብ በምርቱ ውጤታማ ለመኾን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግሯል። ከአንድ የማንጎ ተክል እስከ ሦስት ኩንታል ምርት እንደሚያገኝም አንስቷል።
አርሶ አደር ኪዳኔ ጠጅነህ በቋሚ ተክል ምርት ላይ በመሠማራት ባገኙት ገቢ ከ400 በላይ ላሞችን በመግዛት የእንስሳት እርባታ መጀመራቸውን ነግረውናል። በቋሚ ተክል ምርት ላይ የሚከሰት በሽታ በልማታቸው ላይ እንቅፋት እየፈጠረ እንደሚገኝም አርሶ አደሮቹ አንስተዋል።
በቋሚ ተክል ምርት ይበልጥ ውጤታማ በመኾን ለኅብረተሰቡ ምርታቸውን ማቅረብ እንዲችሉ መንግሥት የመድኃኒት አቅርቦት እንዲያሟላላቸውም ጠይቀዋል።
በወረዳው 380 ሄክታር መሬት በተለያዩ የቋሚ ተክል ምርቶች ለማልማት በቁርጠኝነት እየተሠራ እንደሚገኝ የቃብትያ ሁመራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሳሙኤል ሰለሞን ገልጸዋል። ማንጎ፣ ብርቱካን፣ ሎሚ፣ ሙዝ እና ሌሎች የፍራፍሬ ዓይነቶች በወረዳው በስፋት እንደሚለሙ አንስተዋል።
በወረዳው የሚገኙ አርሶ አደሮች አካባቢያቸውን ለማልማት በቁርጠኝነት እየሠሩ እንደሚገኙ ያነሱት አቶ ሳሙኤል ለቋሚ ተክል አምራች አርሶ አደሮች የመድኃኒት አቅርቦትን ለማሟላት የኬሚካል እና የመድኃኒት አቅራቢ ዩኒየኖችን ለማቋቋም በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በዞኑ ከ900 ሄክታር በላይ መሬት በቋሚ ተክል በማልማት ወደ 220 ሺህ ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ መታቀዱን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ ቡድን መሪ እንዳልካቸው አሰፋ ገልጸዋል።
የኬሚካል አቅራቢ ዩኒየኖችን በማቋቋም ለአርሶ አደሩ የጸረ ተባይ ኬሚካል ግብዓቶችን ለማቅረብ ዞኑ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በዞኑ በቋሚ ተክል ምርት ከ2 ሺህ 400 በላይ አርሶ አደሮች ተሳታፊ መኾናቸውንም አንስተዋል።
ዘጋቢ፡- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!