“በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ የሕክምና ግብዓቶችን ለማቅረብ ፈተና ኾኖ ቆይቷል” የሰሜን ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ

21

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሰሜን ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በ2016 በጀት ዓመት አምስት ወራት በነበረው የግብዓት አጠቃቀም እና ቁጥጥር ከጤና ባለሙያዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።

የባለሙያ አለመሟላት እና ያለውን የባለሙያ አቅም ማሳደግ ላይ ችግር መኖሩ በተሳታፊዎች ተነስቷል። በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት መፍጠሩን እና የተገዛው መድኃኒትም ወደ ጤና ተቋማት ለማጓጓዝ ችግር ማጋጠሙ ነው የተነሳው።

የሰሜን ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ደሳለኝ ዳምጤ እንዳሉት ባለሙያው በችግር ውስጥ ኾኖ ማኅበረሰቡን እያገለገለ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይሁን እንጅ በጸጥታው ችግር ምክንያት የሕክምና መሳሪያ፣ መድኃኒት፣ ደም፣ ኦክስጅን እና ሌሎች ግብዓቶችን ለጤና ተቋማት ለማሰራጨት ፈተና ኾኗል ብለዋል።

የግል እና የመንግሥት የመድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች መድኃኒት እያቀረቡ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው በክልሉ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በቂ አለመኾኑንም አንስተዋል። መምሪያው የቀረቡ ግብዓቶችን ላልተፈለገ ዓላማ እንዳይውሉ ክትትል እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት የማይሰጡ የሕክምና መሳሪያዎችን በመጠገን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መኾኑንም አስረድተዋል። የመድኃኒት አሥተዳደሩን ለማዘመንም የጤና ተቋማትን “ዲጅታላይዝድ” የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

የመድኃኒት ባለሙያዎች በቅንነት ማኅበረሰቡን እንዲያገለግሉ እና የቀረቡ ግብዓቶችን በፍትሃዊነት ተደራሽ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። የጤና አገልግሎት ድንበር የለሽ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ማንኛውም አካል የጤና ባለሙያዎች ለሚሰጡት አገልግሎት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የግብዓት አቅርቦት አሥተዳደር ባለሙያ ሙሃባው ተሾመ እንዳሉት የመድኃኒት አቅርቦት እንደ ሀገር ችግር ቢኖርም በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር አቅርቦቱን ይበልጥ ፈታኝ አድርጎታል። የሚቀርቡ ግብዓቶች በወቅቱ ወደ ጤና ተቋማት ተደራሽ እንዲኾኑ በቀጣይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል። በዞኑ 57 ጤና ጣቢያዎች፣ 195 ጤና ኬላዎች እና አራት ሆስፒታሎች ይገኛሉ።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየከተማዋን የውስጥ ለውስጥ መንገድ ችግር ለመፍታት በትኩረት እየሠራ መኾኑን የሳልመኔ ከተማ መሪ ማዘጋጃ ቤት አስታወቀ።
Next articleቋሚ ተክልን በመስኖ ለማልማት በትኩረት እየሠሩ መኾኑን በቃብትያ ሁመራ ወረዳ በመስኖ ልማት ላይ የተሠማሩ አርሶ አደሮች ተናገሩ።