
ደሴ: ታኅሳሥ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን አልብኮ ወረዳ የሳልመኔ ከተማ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ችግር ለመፍታት በትኩረት እየሠራ መኾኑን የከተማዋ መሪ ማዘጋጃ ቤት አስታውቋል።
አቶ አዚዝ በሽር የሳልመኔ ከተማ ነዋሪ ናቸው። በከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ባለመኖሩ በክረምት ወራት በርካታ ችግሮች ያጋጥሟቸው እንደነበር ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል። አሁን ግን መንገዱ በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በመገንባቱ ችግሮች ሊቀረፍ መኾኑን ተናግረዋል።
ወይዘሮ ዙምራ ይመር የከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገድ መገንባት የአካባቢው ሕዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ነበር ብለዋል። መንገዱ ብዙ ጥቅም አለው ያሉት ወይዘሮ ዙምራ የታመሙ እና ነፍሰጡር እናቶችን በቀላሉ ወደ ሕክምና ቦታ ለማድረስ እና አስፈላጊ ሸቀጣ ሸቀጦችን ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ ያስችላል ነው ያሉት፡፡ ያልተጠናቀቁ መንገዶች እንዲጠናቀቁም ጠይቀዋል፡፡
የሳልመኔ ከተማ መሪ ማዘጋጀት ቤት ሥራ አስኪያጅ ኑረዲን መሐመድ የውስጥ ለውስጥ መንገድ መገንባቱ የነዋሪውን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግር እንደሚቀርፍ ገልጸዋል፡፡ የማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሥራውን በአጭር ጊዜ እንድናጠናቅቅ እድል ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡
አካባቢው አንጻራዊ ሰላም ያለበት በመኾኑ የመንገድ ቆረጣ ሥራው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ይኾናል ያሉት ደግሞ የወረዳው ከተማ እና መሠረተ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኑሩ አሊ ናቸው።
ዘጋቢ:- አንተነህ ፀጋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!