ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር መቻላቸውን በቃብትያ ሁመራ ወረዳ በመስኖ ልማት የተሠማሩ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

37

ሁመራ: ታኅሳስ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ወጣት ልዩነህ ምትኩ በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በቃብትያ ሁመራ ወረዳ በብዓከር ከተማ በመስኖ ልማት ሥራ ላይ ተሰማርቷል።

ከአምስት ዓመት በፊት የመስኖ ሥራን ሲጀምር ከቤተሰብ አነስተኛ ብር በመቀበል ወደ መስኖ ሥራ መግባቱን የተናገረው ወጣት ልዩነህ ዓመቱን ሙሉ ጠንክሮ በመሥራት አምስት የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን፣ በከተማ ውስጥ የመኖሪያ ቤት እና ሌሎች ለመስኖ ግብዓት የሚያስፈልጉ ቁሶች ማሟላት መቻሉን ነግሮናል።

ወጣቱ በስምንት ሄክታር መሬት በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ እያለማ እንደሚገኝ አንስቷል። አሁን ላይ የተሻለ ገቢን በማግኘት በጥሩ የኑሮ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተናገረው ወጣት ልዩነህ በሥሩ ለስድስት ቋሚ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። በቀን ከ15 በላይ ለሚኾኑ ጊዜያዊ ሠራተኞች በመስኖ ልማቱ የሥራ እድል መፍጠሩንም ይናገራል።

አርሶ አደር አብራራው አወቀ በመስኖ ልማት ሦስት ዓመታትን በመሥራቱ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገልጿል። አሁን ላይ የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን ከመግዛት ባሻገር የከተማ ቤት መግዛት መቻሉን አስረድቷል።

ለሁለት ወንድሞቹ እና በቀን ከ10 በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ እድል እንደፈጠረም ነግሮናል። አርሶ አደሮቹ በተሠማሩበት ሥራ ይበልጥ ውጤታማ መኾን እንዲችሉ መንግሥት የነዳጅ እና የማዳበሪያ አቅርቦት እንዲያሟላላቸውም ጠይቀዋል።

በቃብትያ ሁመራ ወረዳ በ2016 የምርት ዘመን ከ2 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ1 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን የቃብትያ ሁመራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሳሙኤል ሰለሞን ገልጸዋል። በወረዳው የመሥራት ቁርጠኝነት ኑሯቸው የመስኖ መሬትን ተከራይተው የሚያለሙ ወጣቶችን የመሬት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

በዞኑ ከ5 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት ጊዜያዊ ተክል በመስኖ በማልማት እና ወደ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ መታቀዱን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ ቡድን መሪ እንዳልካቸው አስፋ ገልጸዋል።

ለመስኖ ተጠቃሚዎች የማዳበሪያ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ3 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮቹ ተደራሽ መኾኑን አንስተዋል።

ከክልል ግብርና ቢሮ ጋር በመነጋገር 50 ጄኔሬተሮች ለአርሶ አደሩ ተደራሸ መኾኑንም አንስተዋል። በመስኖ ልማት የተሠማሩ አርሶ አደሮች የነዳጅ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ከዞኑ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው ብለዋል። በዞኑ ከ4 ሺህ 300 በላይ አርሶ አደሮች በጊዜያዊ ተክል የመስኖ ልማት ሥራ ላይ ተሠማርተው እንደሚገኙ አቶ እንዳልካቸው ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡- ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article56ኛው የአፍሪካ የፋይናንስ፣ የፕላን እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች ጉባኤ በዝምባዌ ይካሄዳል።
Next articleየከተማዋን የውስጥ ለውስጥ መንገድ ችግር ለመፍታት በትኩረት እየሠራ መኾኑን የሳልመኔ ከተማ መሪ ማዘጋጃ ቤት አስታወቀ።