56ኛው የአፍሪካ የፋይናንስ፣ የፕላን እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች ጉባኤ በዝምባዌ ይካሄዳል።

40

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ አዲሱን በቅርቡ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ኾነው የተሾሙትን ክላቨር ጋቴቴን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ እና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊው ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ግንኙነታቸውን አጠናክረው አብረው በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአፍሪካውያን የጋራ ድምጽ በዓለም መድረክ እንዲሰማ በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ኢትዮጵያ እድገት እና ልማቷን ለማፋጠን የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳን ጨምሮ የተለያዩ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ አሕጉር ደረጃ የኢኮኖሚ ዕድገት በማምጣት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር በትብብር እንደምትሰራም አረጋግጠዋል፡፡

የወቅቱ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሺየቲቭ ሊቀመንበር የኾኑት የገንዘብ ሚኒስትሩ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጎልበት እንሰራለን ነው ያሉት። ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ተቋማትን እና ሀገራትን ያቀፈ ኢኒሺየቲቭ እውን እንዲኾን ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር በጥምረት ለመስራት ዝግጁ መኾናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ በበኩላቸው ስለኢትዮጵያ ብዙ ማወቅ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተቋቋመው ለአፍሪካውያን በመኾኑ አፍሪካውያን በዓለም መድረክ የጋራ ድምጻቸው እንዲሰማ በቅንጅት መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ የፋይናንስ፣ የፕላንና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች 56ኛው ጉባኤ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዘጋጅነት በዚምባቡዌ የሚካሄድ መኾኑ በውይይቱ ወቅት ተጠቁሟል።
ጉባኤው ወደ አሳታፊና አረንጓዴ ኢኮኖሚ የሚደረገውን ጥረት በገንዘብ የሚደገፍበት ሂደት ላይ እንደሚመክር ታውቋል ሲል የዘገበው ኢፕድ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኽምጠ ዊከ ጋዜጠ ኽደር 30/2016 ዓ.ስ
Next articleለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር መቻላቸውን በቃብትያ ሁመራ ወረዳ በመስኖ ልማት የተሠማሩ አርሶ አደሮች ተናገሩ።