
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሕዝብ ወኪሎች አሁን ላይ በየአካባቢያቸው ያለውን አንፃራዊ ሰላም ማስቀጠል በሚያስችል ኹኔታ ላይ ከክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ምክክር አድርገዋል።
መድረኩን የመሩት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አሥተባባሪና የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው ሐምሌ መጨረሻ ጀምሮ በተፈጠረው የሰላም እጦት የክልሉ ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ፈተና ውስጥ ቆይቷል ብለዋል።
በመከላከያ ሠራዊትና በሕዝቡ ትግል የተጋረጠው ማኅበራዊና ሁለንተናዊ ቀውስ እየተቀለበሰ እንደሚገኝ አንስተዋል። አሁንም ወደ ተሟላ ሰላም እንድንመጣና ሕዝቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ነበረበት ሰላም እንዲመለስ ለሰላም በር መክፈት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ የአዊ ሕዝብ ከታሪክ ሥልጣኔው ወደ ኋላ ሊመለስ አይገባም፤ ታሪኩን ለማበላሸት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ብቅ ብቅ የሚሉ የተዛቡ አስተሳሰቦችን በቆየ ጠንካራ ባሕሉ መታገል እንደሚገባው ገልጸዋል። ችግሮችን ለመፍታትም አመራሩ ከሕዝብ ጋር መሥራት እንደሚገባው ነው ያስገነዘቡት።
በግጭቶች የተፈናቀሉ ወገኖችም ወደ ቀያቸው ተመልሰው በሰላም እንዲኖሩ ለማስቻል በትብብር የተጀመረው የመመለስ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። የክልሉ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች እንዲመለሱ የተጀመረው አበረታች ጅማሮ ዳር እንዲደርስ ሕዝቡ እንዲተባበር ኀላፊዋ ጥሪ አቅርበዋል።
የተፈጠረው የፀጥታ ችግር የሕዝቡን ጠንካራ ታሪክ እንዳያጎድፍ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ያስገነዘቡት ደግሞ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዶክተር ዘሪሁን ፍቅሩ ናቸው።
የክልሉ መንግሥት የክልሉን ከፍታ ለመመለስ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደኾነም ገልጸዋል። ክልሉ ከዚህ በላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንዳይደርስበት ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን መቆም እንደሚገባውም አሳስበዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ድረስ ሳህሉ የፖለቲካ ነጋዴዎች ከሕዝቡ ውስጥ ገብተው አንድነትን ለማጥፋት እየሠሩ በመኾኑ ሕዝቡ ለጉዳዩ ትኩረት ሠጥቶ መታገል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በምክክር መድረኩ የተሳተፉ የሕዝብ ወኪሎችም አሁን ያለውን አንፃራዊ ሰላም የተሟላ ለማድረግ እና አብሮነትን በማጠናከር ለሰላም መረጋገጥ እንደሚሠሩ ማረጋገጣቸውን ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!