በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የበጋ መስኖ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በወፍላ ወረዳ ተካሄደ።

48

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወፍላ ወረዳ አዲጎሎ ቀበሌ የበጋ መስኖ ልማት በይፋ ተጀምሯል።

የበጋ መስኖ ልማቱን በይፋ ያስጀመሩት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ አዲሱ ወልዴ እንደገለጹት በዞኑ ሦስት ወረዳዎች የተከሰተውን ድርቅ ለማካካስ የበጋ መስኖ ልማት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

አቶ አዲሱ ወልዴ እንደገለጹት በዞኑ 1ሺህ ሄክታር ለማልማት ታቅዶ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 223 ሄክታሩ በበጋ መስኖ ስንዴ ተሸፍኗል።

35 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱንም ተናግረዋል አቶ አዲሱ። ለዚህም ዛሬ በወፍላ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴን በኩታ ገጠም ለማልማት ማስጀመራቸውን ተናግረዋል።

የወፍላ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብርሃም ታፈረ በወፍላ ወረዳ በበጋ መስኖ ለማልማት ከታቀደው 250 ነጥብ 87 ሄክታር ውስጥ 180 ሄክታሩን በስንዴ ኩታገጠም መሸፈን መቻሉንም አስገንዝበዋል፡፡

ዛሬ በአዲጎሎ ቀበሌ 35 ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር ለመሸፈን ሥራው መጀመሩንም ነው የተናገሩት፡፡ በማስጀመሪያ ልማቱም 128 አርሶ አደሮች ተሳታፊ መኾናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
የአዲጎሎ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር መሰለ ኩርፋይ “እስከዛሬ ድረስ በበጋ መስኖ አልምተን አናውቅም” ነው ያሉት፡፡

በዘንድሮው ዓመት መንግሥት የሰጣቸውን ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ተጠቅመው የተሻለ ምርት ለማግኘት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ልማቱ መግባታቸውንም ተናግረዋል።
አርሶ አደር ዘርዓይ ካህሳይ ባለፋት ዓመታት የደቀቀው ኢኮኖሚያቸውን ለማካካስ በበጋ መስኖ በኩታገጠም ማልማት ፋይዳው ላቅ ያለ ነው ብለዋል።

መንግሥት የጄኔሬተር፣ የማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደር ዘርዓይ “ከ3 ሄክታር ማሳዬ እስከ 90 ኩንታል ለማግኘት አቅጄ እያለማሁ ነው” ብለዋል።

በወፍላ ወረዳ የበጋ መስኖ ልማት ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ እና የወፍላ ወረዳ የሥራ ኀላፊዎች እና የአዲጎሎ ቀበሌ አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሀገራዊ ምክክሩ አካል ጉዳተኞች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ እየተሠራ መኾኑን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን አስታወቀ።
Next article“የአዊ ሕዝብ በአብሮነትና በታታሪነት የሚታወቅ ነው” አቶ ደሳለኝ ጣሰው