
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን አካል ጉዳተኞች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካና የሀሳብ መሪዎች እንዲሁም በኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለውን ልዩነት በምክክር ለመፍታት በ2014 ዓ.ም ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።
አሁን ላይም ኮሚሽኑ በ700 ወረዳዎች ተሳታፊዎችን የመለየትና የአጀንዳ ሀሳብ የሚሰጡ ተወካዮቻቸውን በመምረጥ ላይ የሚገኝ ሲሆን በአማራ እና ትግራይ ክልል ተሳታፊዎችን ለመለየት ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ገልጿል። በቅርቡም ኮሚሽኑ የአጀንዳ ሀሳቦችን ወደ ማሰባሰብ ምዕራፍ እንደሚሸጋገር ተመላክቷል።
ሀገራዊ ምክክር የታለመለትን ግብ እንዲያሳካ ኮሚሽኑ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን በተደጋጋሚ የሚገለጽ ሲሆን ይህንን መነሻ በማድረግ ኢዜአ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽንን አነጋግሯል።
የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ ለሰላም መደፍረስ ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮችን በውይይት እልባት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። ከዚህ አንጻር ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን ጠቁመው ለምክክሩ ውጤታማነት የሁሉም ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ፌዴሬሽኑ አካል ጉዳተኞች በምክክሩ ንቁ ተሳተፊ በመሆን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የሚያስችሉ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። ኮሚሽኑ በተለያዩ አደረጃጀቶች የሚያከናውናቸው ሥራዎችም አካል ጉዳተኞችን ያካተተ እንዲሆን ከኮሚሽኑ ጋር የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።
በቀጣይም ምክክሩን ስኬታማ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አካል ጉዳተኞች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!