
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል 450 ሺህ አርሶ አደሮች እና ሦስት ባለሃብቶች በቡና ልማት ላይ ተሰማርተዋል። 21 የቡና መሰረታዊ ማኅበራት እና አንድ ዩኒየን ደግሞ የቡና ግብይቱን እያካሄዱ ነው።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልት እና ፍራፍሬ ከፍተኛ ባለሙያ አወቀ ዘላለም በክልሉ 28 ሺህ ሄክታር ቡና እንደለማ ገልጸዋል። በየዓመቱም 2 ሺህ 500 ሄክታር ማሣ ላይ 7 ሚሊየን የቡና ችግኝ እየተተከለ ነው ብለዋል።
ይህንን ለቡና ምቹ የኾነ ተፈጥሮ በመጠቀም የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን በአውሮፓ ሕብረት – ካፌ ፕሮጀክት የሚደገፍ ቡና አምራች አርሶ አደሮችን በመስክ ለማስተማር የአሠልጣኞች ሥልጠና በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው። በሥልጠናው አርሶ አደሮች ቡናን በተሻሻለ ዘዴ ለማምረት የሚማማሩበትን አሠራር የሚያመቻቹ እና የሚያሠለጥኑ የቀበሌ ባለሙያዎች ይሳተፉበታል።
አቶ አወቀ በክልሉ የቡና ማምረት አቅም ባላቸው 21 ወረዳዎች በአርሶ አደሮች እና ባለሃብቶች ቡና እየተመረተ መኾኑን ገልጸዋል። “በየዓመቱ ከ130 ሺህ ኩንታል በላይ ቡና እናመርታለን፤ በየዓመቱ 2 ሺህ 500 ኩንታል ቡና ወደ ውጪ መላክ ጀምረናል” ነው ያሉት
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባንጃ ወረዳ የአስኩና አቦ ቀበሌ የመስኖ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ባለሙያ የመንግሥት ፈጠነ በቀበሌዋ 160 ሄክታር በላይ መሬት በቡና ችግኝ እንደተሸፈነ ገልጸዋል። ወይዘሮ የመንግሥት በቀበሌው ውስጥ ከሚኖሩ ከ970 በላይ አርሶ አደሮች ከ710 በላይ አርሶ አደሮች ቡና በማልማት ላይ መሠማራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በሄክታር እስከ 4 ኩንታል ቡናም ይመረታል። ፕሮጀክቱ ከጀመረ ወዲህ አርሶ አደሮች ቡና በማልማት የበለጠ ተጠቃሚ መኾናቸውን አብራርተዋል፡፡
በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ የተክለን ቀበሌ የሰብል ልማት ባለሙያ ቻላቸው ሞላ በቀበሌው 12 ሄክታር ማሣ ላይ ቡና እየለማ መኾኑን ገልጸዋል። ልማቱ የአውሮፓ ሕብረት ፕሮጀክት በመጀመሩ እየተስፋፋ እንደኾነም ተናግረዋል። አርሶ አደሮች ተደራጅተው በዘመናዊ የቡና ልማት ላይ እየተማማሩ ነው። ሥልጠናው ከተጀመረ ወዲህም ግንዛቤ እየተፈጠረላቸው ለገበያ ለማምረት ጥረት እያደረጉ መኾኑን ገልጸዋል። ሥልጠናው ከሰሜን ጎጃም እና ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሁለት ወረዳዎችን እንደሚያካትት ታውቋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!