ሴቶች በኢትዮጵያ መስኖ ፕሮጀክት ተጠቃሚ አለመኾናቸው ተገለጸ፡፡

24

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንዲሁም ከዓለም አቀፉ ልማት እና ግምገማ ማኅበር ጋር በመተባበር በሰራባ የመስኖ ፕሮጀክት፣ በምዕራብ እና ምሥራቅ ደንቢያ ወረዳዎች ላይ ትኩረት እድረጎ ጥናት ሠርቶ አቅርቧል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናቱ አስተባባሪ ዶክተር ተፈራ ቢተው እንዳሉት ጥናቱ በሰራባ መስኖ ፕሮጀክት በምዕራብ እና በምሥራቅ ደንቢያ ወረዳዎች ተጠቃሚ የኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ጥናቱ ከውጭ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እንደተሠራም አስረድተዋል።

በመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር የመስኖ ፕሮጀክቶች ዝግጅት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ሳሙኤል ሁሴን እንዳሉት ኢትዮጵያ 10 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለመስኖ ምቹ የኾነ አቅም አላት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 2 ሚሊዮን ሄክታር ብቻ እየለማ ያለ መኾኑንም አስረድተዋል።

ኢንጅነር ሳሙኤል “ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ያሉ ክፍተቶችን በማጥናት እና በመለየት የቀጣይ ልማቶች ላይ እንዲተኮር እያደረግን እንገኛለን” ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተያዘው የፈረንጆቹ 2023 ዘመን የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየሠራች እንደምትገኝም ተገልጿል። ይህ የምግብ ዋስትናም ወሳኝ እና ራስን የመቻል ገጽታ እንደኾነም አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች የሥነ ምግብ ስብጥርን ማረጋገጥ እና የሴቶችን አቅም ማጎልበት በሚል ጥናት ቀርቧል። የጥናት ቡድኑ መሪ መልካሙ ወርቄ በጥናቱ በተለይም ሴቶች ከመስኖ ፕሮጀክቱ ብዙም ተጠቃሚዎች አይደሉም ብለዋል። መስኖ በምግብ ስብጥርን በማምጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢኖረውም ሴቶች በፕሮጀክቱ ላይ ተጠቃሚነታቸው ዝቅተኛ መኾኑንም አንስተዋል።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዋንጫ ተፎካካሪነትን ለማጠናከር እና ከወራጅ ቀጣና ለመራቅ ኤቨርተን ከማንቸስተር ሲቲ የሚደረግ ትንቅንቅ፡፡
Next article“የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪ ሃብቱን አክብሮ በመያዙ የኢንደስትሪ ፍሰቱ እየጨመረ መጥቷል” አቶ እንድሪስ አብዱ