
ዛሬ በጉዲሰን ፓርክ ኤቨርተን ከማንቸስተር ሲቲ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡ ማንቸስተር ሲቲ ከ17 ጨዋታዎች 10ሩን አሸንፏል፤ በአራት አቻ ወጥቶ በሦስቱ ተሸንፎ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ34 ነጥብ ደረጃው 5ኛ ነው፡፡
ኤቨርተን ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ባደረጋቸውን ያለፉት 20 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በአንዱ ብቻ ነው። የኤቨርተኑ አለቃ ሴያን ዲያች ከማንቸስተር ሲቲው ፔፕ ጋርዲዮላ ጋር ያደረጋቸውን 13 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በ12ቱ ተሸንፈዋል።
ማንቸስተር ሲቲ የዓለም የክለቦች ዋንጫን ባሸነፈ ሰሞን ይህን ጨዋታ በማድረጉ በራስ የመተማመን ስሜቱን ከፍ ያደርግለታል፤ ጋርዲዮላ እና ተጫዋቾቹ በሊጉ ዋንጫ ላይ ይበልጥ እንዲያማትሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለኾነም ማንቸስተር ሲቲ ካሸነፈ የዋንጫ ተፎካካሪነቱን ያጠናክርለታል፡፡
ኤቨርተን በፊናው 18 ጨዋታዎችን አድርጎ በስምንቱ በማሸነፍ፣ በሁለቱ አቻ ወጥቶ እና በስምንቱ ተሸንፎ እንዲሁም 10 ነጥብ ተቀንሶበት 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ኤቨርተን ከረታ ከወራጅ ቀጣናው ቀዩ መስመር ላይ ለመራቅ ያግዘዋል ሲል ዴይሊ ሜይል ስፖርት በድረ ገጹ ጽፏል፡፡
የኤቨርተኑ አለቃ ሴያን ዲይች “በሜዳችን እና በደጋፊዎቻችን ፊት ማንቸስተር ሲቲን አሸንፈን ደረጃችንን ለማሻሻል እንጫወታለን፤ ልጆቼ አያሳፍሩኝም” ማለታቸውን ዴይሊ ሜይል ጽፏል፡፡ በኦፕታ ሱፐር ኮምፒውተር የቅድሚያ የጨዋታ ግምት መሰረት ኤቨርተን 37 ነጥብ 9 በመቶ የማሸነፍ እድል ተችሮታል፡፡
የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ እንዳሉት አማካኙ ሮድሪ በፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ጉዳት እንዳጋጠመው አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና ልጁ የመሰለፍ ተስፋ እንዳለው ተናግረዋል።
ጋርዲዮላ አክለውም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ኤርሊንግ ሃላንድ የእግር ህመም ገጥሞታል “ግን ‘ይሰለፋል፤ አይሰለፍም ብላችሁ አትጠይቁኝ’ ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የኦፕታ ሱፐር ኮምፒውተር ማንቸስተር ሲቲ ከኤቨርተን በጉዲሰን ፓርክ የሚያደርገውን ጨዋታ 62 ነጥብ 1 በመቶ ያሸንፋል ሲል ትንበያውን አስቀምጧል፡፡
ዛሬ በእንግሊዝ ፕሪሜየር ሊግ ሌሎች ጨዋታዎችም ይደረጋሉ፤ ብሬንትፎርድ ከዎልቭስ፤ ቼልሲ ከክሪስታል ፓላስ ይጫወታሉ፡፡ በትናንት ጨዋታዎች ኖቲንግሃም ኒውካስትልን 3ለ1፤ በርንማውዝ ፉልሃምን 3ለ0፤ ሉተን ሸፊልድን 3ለ2፤ ሊቨርፑል በርንሌይን 2ለ0፤ ማንቸስተር ዩናይትድ አስቶን ቪላን 3ለ2 አሸንፈዋል፡፡
ፕሪሚየር ሊጉን ሊቨርፑል በ42 ነጥብ ይመራዋል፡፡ አርሰናል በ40 ነጥብ ይከተላል፤ አስቶን ቪላ በ39 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ይገኛል ሲል ቢቢሲ ስፖርት በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
ዘጋቢ፡-ሙሉጌታ ሙጨ