
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የገና እና የጥምቀት በዓላትን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር በቂ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል። የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ እንደገለጹት የታኅሣሥ እና ጥር ወራት በርካታ ዓለም ዓቀፍ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡባቸው ወቅቶች ናቸው። በተመሳሳይም የገና እና የጥምቀት በዓልን ተከትሎ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ፍሰት ይጨምራል።
ሁለቱ በዓላት ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በስፋት የሚከበሩ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል።
በዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጎብኝዎች ወደተለያዩ ቦታዎች በመሄድ መጎብኘት እዲችሉ የቱሪስት መዳረሻዎቹ ክፍት ሆነው አገልግሎት እንዲሰጡ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ለአብነትም ከገና በዓል ጋር በተያያዘ ወደ ላሊበላ ከተማ በርካታ ጎብኝዎች የሚሄዱ በመሆኑ ከከተማዋ ከንቲባና ከቤተ ክርስቲያኑ አሥተዳዳሪ ጋር ውይይት መደረጉን አንስተዋል።
ወደ አካባቢው የሚሄዱ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎችን ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደተቻለም አብራርተዋል።
አቶ ስለሺ ለኢፕድ እንደገለጹት በዓላቱ በስፋት በሚከበርባቸው ቦታዎች የመጓጓዣ ችግር እንዳይኖር እና ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በቂ የአውሮፕላን በረራዎች እንዲኖሩ በጋራ እየተሠራ ይገኛል።
በዓላቱን ምክንያት አድርገው የሚመጡ ቱሪስቶችም አማራጭ የጉብኝት ጥቅሎች እንዲኖር እንደሚደረግ ገልጸዋል። ይህን ለማሳካትም አስጎብኝ ድርጅቶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ሁለቱ በዓላት በሌላው ዓለም በስፋት የማይከበሩ ናቸው። በተጨማሪም አብዛኛው የዓለም ሀገራት በአሁኑ ሰዓት አዲስ ዓመትን ተከትሎ እረፍት ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም ከምንጊዜውም በላይ የውጭ ቱሪስቶች ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል። በዘንድሮ የገናና ጥምቀት በዓልም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ ጎብኝዎች ወደ ሀገሪቱ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ከጸጥታ ጋር ተያይዞ ያለውን ስጋት ለመቅረፍ ቱሪስቶች በኦንላይን መረጃ ማግኘት የሚችሉበትን የሞባይል መተግበሪያ በማልማት ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው። በተጨማሪም ሰዎች በአካል መረጃ ማግኘት የሚችሉበትን የመረጃ ማዕከል በቦሌ አየር ማረፊያ ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
እንደ ሀገርም የቱሪስቱን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም በአሁኑ ሰዓት ሰፊ እድል አለ ሲሉ ገልጸዋል። የገበታ ፕሮጀክቶችም ለዚህ ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል። አክለውም በዓላት ምክንያት በማድረግም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር እንዲገቡ ጥሪ የሚደረግ ይሆናል ሲሉ ተናገረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!