‘ቻይና እና ሕንድ ከሚታተሙ መጽሐፍት በተሻለ ጥራት ማተም እንችላለን” ዓባይ የህትመት እና የወረቀት ፓኬጂንግ ፋብሪካ

64

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይ የህትመት እና ወረቀት ፓኬጂንግ ፋብሪካ በ2010 ዓ.ም የተቋቋመ የተለያዩ ህትመቶችን የሚሠራ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው።

የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ ታደሰ መላሽ ህትመቶችን በተለይም መማሪያ መጻሕፍትን በማተም የትምህርት ሥርዓቱን ለማገዝ የተቋቋመ ፋብሪካ መኾኑን ገልጸዋል። የጋምቤላ እና የአዲስ አበባን ህትመቶች መሥራቱን እና አሁን ደግሞ የአማራ ክልል የትምህርት ህትመቶችን እየሠራ መኾኑንም ተናገረዋል።

ፋብሪካው ለ150 ወጣቶች ቋሚ እና 52ቱ ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። የውጭ ሀገር ህትመትን በማስቀረት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ እና ግብር በመክፈል ለሀገር ልማት እያገዘ ነው። ትርፍ ሲገኝም መልሶ ለልማት በመስጠት ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል።

ፋብሪካው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በምሥራቅ እና በመካከለኛው አፍሪካ የዘርፉ መሪ መኾኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

ጥሬ ዕቃ ከውጭ ለማስገባት የምንዛሬ እጥረት እያጋጠመን ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ ”መጽሐፍ ለማስገባት የሚፈቀደው የውጭ ምንዛሬ ለእኛ ጥሬ ዕቃ ለማስገባት አይፈቀድም” ብለዋል። ይህ አሠራር መስተካከል እንደማገባውም ጠቁመዋል። “ጥሬ ዕቃው የሚገኝበት እድል ከተመቻቸ ቻይና እና ሕንድ ከሚታተሙ መጽሐፍት በተሻለ ጥራት ማተም እንችላለን” ሲሉም ተናግረዋል። በቅናሽ ዋጋ እና በብዛት ለማምረትም እድል ይሰጣል ብለዋል። መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፋብሪካውን ሲጎበኝ ያገኘነው የአማራ ክልል የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ሠራተኛ ወጣት ማሞ ማርማር ”ፋብሪካው በዚህ ልክ እንደተደራጀ አላውቅም ነበር” ብሏል።
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ባለሙያው አለኸኝ መልካሙ ፋብሪካው የአዲሱን ሥርዓተ ትምህርት መጻሕፍት እያተመ መኾኑን ተናግረዋል።

አቶ አለኸኝ ”ያስቸገረን የበጀት እጥረት እንጂ የህትመት ሥራው አይደለም” በማለትም የዓባይ የህትመት እና የወረቀት ፓኬጂንግ ፋብሪካ በጥራት እና በፍጥነት እንደሚሠራላቸው ተናግረዋል።

ፋብሪካውን የትምህርት፣ የሥራ እና ሥልጠና እንዲኹም የአማራ ክልል የሙያ ብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ ኤጀንሲ አመራሮች እና ሠልጣኝ ሠራተኞች ጎብኝተውታል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የምግብ ሉዓላዊነታችንን አስተማማኝ በኾነ መልኩ ለማረጋገጥ የምናረገው ጥረት እየተሳካ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየገና እና የጥምቀት በዓላትን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር በቂ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።