
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ተመስገን ጥሩነህ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ሥታዲየምን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
የስታዲየሙን የሥራ እንቅስቃሴ ለመሪዎቹ ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ የባሕር ዳር ስታዲየም የካፍን ደረጃ እንዲያሟላ ኾኖ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም ከአሁን በፊት የካፍን ደረጃ አላሟላም በሚል ከአህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች መከልከሉ ይታወሳል።
ስታዲዬሙ በሁለት ምዕራፍ እንደሚጠናቀቅ የተናገሩት ኀላፊው የመጀመሪያው የግንባታ ሥራ ተጠናቅቋል ብለዋል። ባለፈው ዓመት የተጀመረው ሥራም መቀጠሉን ገልጸዋል።
የሜዳው የሳር ተከላ ሥራ በቅርቡ እንደሚጀምርም ተናግረዋል። የሚተከለው ሳር እና የሜዳው የውኃ ማፋሰሻ ቱቦ ደረጃውን የጠበቀ መኾኑም ተመላክቷል። ስታዲየሙን ደረጃውን የጠበቀ አድርጎ የመሥራቱ ሥራ መቀጠሉንም ተናግረዋል።
ካፍ ስታዲየሙ ደረጃውን የጠበቀ እንዲኾን 17 መመሪያዎችን አስቀምጧል ሲሉም ቢሮ ኀላፊው አብራርተዋል። ካፍ ያስቀመጠውን መሥፈርት ለማሟላት ነው ሥራዎች እየተከናወኑ ያሉትም ተብሏል። አሁን የተጀመሩት ሥራዎች ሲጠናቀቁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሀገሩ የመጫወት እድል ያገኛል ተብሏል። ለከተማዋም የስፖርት ቱሪዝም እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!