የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ከዩኒኖች እና የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ሥራ መጀመሩን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

28

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ለሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት 60 ሚሊየን ብር መመደቡን እና ወደ ሥራ መግባታቸውን ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በሰላም እጦት ምክንያት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቀነስ ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።

አቶ ጎሹ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመቅረፍ የጸጥታ መዋቅሩን የማደራጀት፣ የማጠናከር እና የማሠልጠን ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የከተማዋ ሰላም መሻሻሉን አንስተዋል። የኅብረተሰቡ ተሳትፎም ወሳኝ በመኾኑ ሕዝቡን ለማሳተፍ እየተሠራ እንደኾነ አክለዋል።

ከሰላም ማስፈኑ ጎን ለጎን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን መፍታት መጀመሩን ከንቲባው ገልጸዋል። ቆመው የነበሩ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡

21 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ እየተገነባ መኾኑን ያወሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይም ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት አድርገናል ነው ያሉት፡፡ ከውይይቱም በመነሳት ችግርችን ለመፍታት እርምጃዎችን መውሰድ ጀምረናል ብለዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ለሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት 60 ሚሊየን ብር መመደቡን ገልጸዋል። ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ከዩኒኖች እና የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ሥራ መጀመሩን አንስተዋል፡፡

የቤት ኪራይ መጨመርን ለመከላከል የከተማ አሥተዳደሩ ደንብ ማውጣቱን ያሳወቁት ከንቲባው ተግባራዊነቱም ክትትል እንደሚደረግበት ነው የጠቀሱት።
የመንግሥት ሠራተኛው ህሊናውንም እጁንም ንጹሕ አድርጎ በማገልገል ኅብረተሰቡን ከችግር ለመታደግ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መንግሥት ለክልሉ ችግር መፈታት የሰላም ጥሪ ማቅረቡን ከንቲባው ጠቅሰው ”በተለያዩ ምክንያቶች የወጡ ወንድሞቻችን በሰላም ተመልሰው ክልላችን እና ሀገራችንን በጋራ የምናለማበት ሁኔታ መፍጠር ይገባናል” ብለዋል።

ለአማራ ሕዝብ ጥያቄ ሁላችንም ባለቤቶች ሆኾን በጋራ መመካከር ነው የሚያስፈልገን ሲሉም አክለዋል። ሰላማችን ወደነበረበት ተመልሶ፣ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሙሉ ጊዜ ሥራ በማስገባት ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴው እንዲነቃቃ ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኃይል አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሠጥቶ ይሠራል” የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን
Next articleከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን የሥራ እንቅሥቃሴ ተመለከቱ።