
ጎንደር: ታኅሳስ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጎንደር ከተማ የሚገኙ የኢንቨስትመንት ተቋማት በከተማዋ ያለውን የተሻለ ሠላም ተጠቅመው በሥራ ላይ ኾነው መመልከታቸውን የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ከሠላም ማስከበሩ ጎን ለጎን ኢንቨስትመንቱን እንደሚደግፍ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ገልጸዋል። የኃይል አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሠጥቶ ይሠራልም ብለዋል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድሩ፡፡
በጎንደር ከተማ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ያሉ 189 ኢንቨስትመንቶች በአምስት ኢንዱስትሪ መንደሮች በሥራ ላይ እንደሚገኙ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ግርማየ ልጃለም ገልጸዋል።
አልሚዎቹ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያላቸው ባለሃብቶች መኾናቸውን ያነሡት መምሪያ ኀላፊው ለአስር ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል ተፈጥሯልም ብለዋል። በከተማዋ ያሉ ኢንዱስትሪዎች በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች የሚያመርቷቸውን ምርቶች በግብዓትነት የሚጠቀሙ መኾናቸውን የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሀይ አብራርተዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ለባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በቂ የመሬት አቅርቦት ማዘጋጀቱንም ገልጸዋል። ቲቲኬ ኢንዱስትሪ የምግብ ዘይት እና ሳሙና እያመረተ ቢኾንም በመብራት አቅርቦት ችግር ምክንያት በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ እንዳልገባ የጎንደር ቅርንጫፍ ሥራ አሥኪያጅ አስናቀው ዘውዱ ተናግረዋል።
በዶሮ እርባታ የተሠማሩት ጽላተ ማርያም ተመስገን ዘርፉ አዋጭ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የጸጥታ ሁኔታው የመኖ አቅርቦቱ እና የገበያ ሁኔታው ላይ ተጽዕኖ እንደፈጠረባቸው አንስተዋል።
ዘጋቢ፡- ተስፋዬ አይጠገብ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!