
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዞኑ የበጋ መስኖ ልማት ሥራ በተጠናከረ መልኩ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ዳህና ዋዋ ቀበሌ የሚገኙ አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት ተጠቃሚ መኾናቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል። በሄክታርም ከ45 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁም ነው የገለጹት።
በቀበሌው በሰራባ የመስኖ ፕሮጀክት 827 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ የሚለማ ሲኾን ከ1ሺህ 400 በላይ አርሶ አደሮች በሥራው ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ማንደፍሮ መርሻ በወረዳው ከ3 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።
የምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ወዳጀ ባንቴ አርሶአደሮች በበጋ መስኖ ልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ለማስቻል ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመኾን እየተሠራ ነው ብለዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ንጉሴ ማለደ እስካሁን በተሠራው የመስኖ ልማት እንቅስቃሴ 40 በመቶ የሚኾነው መከናወኑን ተናግረዋል።
በዞኑ 29 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለመሸፈን መታቀዱን የገለጹት ኀላፊው ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ለማግኘት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። እስከ ታኅሣሥ 30/2016 ዓ.ም ድረስ በዘር የመሸፈን ሥራን ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደሚገኝም ከመምሪያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ዘጋቢ፡- ቃልኪዳን ኃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!