የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራን ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቁን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

45

ሰቆጣ ፡ ታኅሣሥ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሉ 11 ወረዳዎች 675 ተፋሰሶች ይገኛሉ። በዘንድሮው ዓመትም 29 አዲስ ተፋሰሶችን ጨምሮ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ለመሥራት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቁን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አሰፋው ታፈረ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ባለፋት ዓመታት በነበረው ጦርነት ምክንያት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ተቀዛቅዞ ቆይቷል፡፡ በዚህ ዓመት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራው ከነበረበት መቀዛቀዝ ወጥቶ በተጠናከረ መንገድ ለማልማት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።

በዞኑ 675 ተፋሰሶችን ለማልማት 140 ሺህ 915 አልሚ የሰው ኀይል እንደተለየም ጠቁመዋል። በአፈር እና ውኃ ጥበቃ፣ በደን ልማት፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ተፋሰሶች የሥራ እድል እንዲፈጠር ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ ስለመኾኑም ነው የነገሩን፡፡ ቡድን መሪው “ከጥር 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ በንቅናቄ ልማቱን ለማስጀመር ተዘጋጅተናል” ብለዋል።

በ2015 ዓ.ም በነበረው የተፈጥሮ ሃብት ልማት እንቅስቃሴ በአትክልት እና ፍራፍሬ፣ በደን ልማት እና በእንሰሳት መኖ ልማት ከ3ሺህ በላይ ለሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሥራ እድል መፍጠር እንደተቻለም አቶ አስፋው ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ሃብትን ማልማት የውዴታ ግዴታ ነው ያሉት ቡድን መሪው ሁሉም አልሚ የዞኑ ማኅበረሰብ ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ ከምታመርታቸው የምርት አይነቶች 5ሺህ 700 ምርቶች በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ላይ ይሁንታ አግኝተዋል” የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር
Next article“የመሠረተ ልማት ሥራዎች በፍጥነት መሠራት አለባቸው” ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ