“ኢትዮጵያ ከምታመርታቸው የምርት አይነቶች 5ሺህ 700 ምርቶች በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ላይ ይሁንታ አግኝተዋል” የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

37

አዲስ አበባ፡ ታኅሣሥ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያን የዓለም ንግድ አባልነት ድርድር እና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ላይ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ 126 ሀገራትን ይዞ እ.ኤ.አ በ1995 የተጀመረው የዓለም ሀገራት የንግድ አባልነት አሁን ላይ 28 ሀገራት ተደራድረው አባልነቱን መቀላቀል ችለዋል።

እ.ኤ.አ 2003 ጀምሮ በታዛቢ አባልነት ስትሳተፍ የቆየችው ኢትዮጵያ አባል ለመኾን 4 ጊዜ ስለመደራደሯ ገልጸዋል፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከአባል ሀገራት ወደ 900 ጥያቄ ቀርቦላት ለመመለስ በየድርድሮቹ ሠርታለች ያሉት ሚኒስትሩ አሁን ላይ 181 ጥያቄ ቀርተዋል ብለዋል።

አባል ለመኾን ለሚደረገው ድርድር በ2020 በአባል ሀገራት የቀረቡ በርካታ ጥያቄዎችን ሁሉ ለመመለስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚመለከታቸውን ሁሉ በማስተባበር ሥራዎችን እየሠራ እንደኾነም አስገንዝበዋል።

ከቀረቡት ጥያቄዎች ውስጥ የታክስ መጠን አንዱ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ ጥያቄውን ለመመለስም በ5ተኛው ድርድር ጥናት ተጠንቶ፣ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየመረመረ ነው ብለዋል፡፡ የሚገኘውን ውጤትም ይዞ በሚቀጥለው ድርድር አባል ለመኾን እንደሚሠራም አስገንዝበዋል።

ሀገሪቱ የዓለም የንግድ አባል መኾኗ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የሚያበረታታ እና አዳዲስ አሠራር እንዲፈጥሩ የሚያስችል ነው ብለዋል። የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነትን በተመለከተ 47 ሀገራት ወደ ስምምነቱ የየራሳቸውን እቃ ይዘው መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደሀገር ከምታመርታቸው 6ሺህ 800 የምርት አይነቶች ውስጥ 5ሺህ 700ዎቹ በ10 ዓመት ነፃ እንዲኾኑ አቅርባ ይሁንታን ማግኘቷን ነው ያብራሩት፡፡ ይህም ከምርቶቹ ውስጥ 90 በመቶ ይሁንታን ማግኘት እንደተቻለ አስገንዝበዋል።

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አሁን የሚቀረው የሙከራ ሥራ መጀመር ነው ብለዋል፡፡ “ይህን እምንገልጸው የግሉ የንግድ ማኅበረሰብ እና የሚመለከታቸው አምራቾች እንዲሁም ሌሎች እንዲዘጋጁ ለማድረግ ነው” ብለዋል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ።

ዘጋቢ፦ አብነት እስከዚያ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀገራዊ ምክክሩ በተፈለገው ጊዜ እንዲጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል” አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ
Next articleየተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራን ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቁን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታወቀ።