
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ካለፉት አራት ወራት ወዲህ በአማራ ክልል ውስጥ በተከሰተው የሠላም እጦት በክልሉ በርካታ የልማት ሥራዎቻች ስለማስተጓጎሉ የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ገልጿል። ገበሬው ምርቱን ለመሰብሰብ፣ ያመረተውን ወደ ገበያ ለመውሰድ እንዲሁም የልማት ተቋማት በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ በመግባት ምርት እና አገልግሎታቸውን ለተጠቃሚው ለማቅረብ ሰላም ያስፈልጋል።
ለእድገታችን ተሥፋ የኾነውን የሕዳሴ ግድብ ጨምር የሚመግበው፣ የባሕር ዳር ከተማም እስትንፋስ የኾነው ጣና ሐይቅ በሠላም አለመኖር ምክንያት ህልውና የባሰ ፈተና ላይ ወድቋል፡፡
በሐይቁ ተፈጥሮ የነበረውን የእምቦጭ አረም ከአካባቢው እስከ ሀገር አቀፍ፣ ከዚያም አልፎ ዓለም አቀፍ ንቅናቄ በመፍጠር ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ችግሩን መቀነስ ተችሎ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡
አረሙ በአንዴ የሚጠፋ ባለመሆኑ ቀጣይ ክትትል የሚጠይቅ ነው። በየጊዜው በክልሉ የሚፈጠሩ የሰላም ችግሮች ሐይቁን ከዚህ ተግዳሮት ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት እየተደናቀፈ ይገኛል፡፡
በ2013 ዓ.ም በህልውና ዘመቻ፣ አሁን ደግሞ በውስጥ በተፈጠረ ሁከት የእምቦጭ አረምን ከሃይቁ ለማስወገድ ፋታ አልተገኘም። “የሰላም እጦት ችግሩ በግጭቱ ከሚደርሰው ጥፋት ባሻገር የዘላቂ ህልውናችን መሰረት በኾነው ጣና ሐይቅ ላይም የከፋ ፈተና ደቅኖበታል” ሲልም ቢሮው በመረጃው አስፏሯል።
የእምቦጭ አረምን ለማጥፋት ሲደረግ የነበረው ጥረት መስተጓጎል ገጥሞታል። ቀደም ሲል በመንግሥት ግዥና በተለያዩ ድጋፎች የመጡት የአረም ማስወገጃ መሳሪያዎች አፈር እየበላቸውና ተበላሽተው ከጥቅም ውጭ እየኾኑ ነው፡፡ ይህንን ተግባር በተልዕኮነት ተቀብሎ የሚሠራው ኤጄንሲም በሠላም ችግር ምክንያት ተንቀሳቅሶ ለመሥራት አልቻለም። አረሙን በተጨባጭ ለማስወገድ ተጀምረው የነበሩ ጥረቶች ሁሉ በክትትል መጓደል ምክንያት ለስኬት አልበቁም። በዚህም ምክንያት አረሙ እንደገና ወደ ከፋ ስጋትነት እንዲመለስ ኾኗል፡፡
በአጠቃላይ በክልላችን የተፈጠረው የሰላም እጦት እያደረሰ ያለው ዘርፈ ብዙ ጉዳት እጅግ ሰፊ ነው፡፡ በመሆኑም በሁሉም ሴክተር ያስከተለው ችግር ተለይቶ ሲታይ በአጭር ጊዜ ውስጥ የደረሰው ውድመት ክልሉን እጅግ ወደኋላ እንዲመለስ እያደረገው ይገኛል፡፡ ስለሆነም ይህንን ስጋት በጥሞና በመገንዝብ እና ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በየአካባቢያችን ሰላም እንዲሰፍን የሰላም አምባሳደር በመኾን በጋራና በአንድነት መንቀሳቀስ አለብን፡፡
ሰላማችንን በማረጋገጥ የክልላችን ብሎም የሀገራችን ሃብት የሆነውን ጣና ሐይቅን ከእንቦጭ አረም ወረራ በጋራ መከላከል ይገባል ሲል የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!