
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በክልሉ የተካሄደውን የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ቆጠራ የጥናት ግኝት ለባለድርሻ አካላት አስተዋውቋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የተፈጥሮ ሀብት መምህር አበበ አስቻለው (ዶ.ር) እንዳሉት በዓለም ላይ በተለያዩ ምክንያቶች በሚለቀቁ የአማቂ ጋዝ ልቀት የአየር ንብረት ለውጥ አስከትሏል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የአማቂ ጋዝ ልቀት መጠን ለማወቅ በ2012 ዓ.ም ጥናት ተደርጎ እንደነበር ነው መምህሩ የገለጹት።
የአማራ ክልል በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የአማቂ ጋዝ ልቀት የማመንጨት አቅም ለማወቅ ዩኒቨርሲቲው ከክልሉ አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ለአንድ ዓመት ያህል ጥናት አካሂዷል። በጥናቱም የግብርናው ዘርፍ 89 በመቶ የሚኾነውን የሙቀት አማቂ ጋዝ በመልቀቅ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ተረጋግጧል። የኢነርጅ ዘርፉ 10 በመቶ የሙቀት አማቂ ጋዝ በመልቀቅ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል። ኢንዱስትሪዎች እና በአካባቢ የሚለቀቁ ቆሻሻዎች ደግሞ ለሙቀት መጨመሩ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸው በጥናቱ ተመላክቷል።
በየጊዜው በሚለቀቁ የሙቀት አማቂ ጋዝ ምክንያት በሚከሰተው የሙቀት መጨመር በሰው ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ባለፈ ለተባይ መራባት እና ለበሽታ መስፋፋት ምክንያት ኾኗል። ለምርት እና ምርታማነት መቀነስም እንደምክንያት ተነስቷል።
ችግሩን ለመቀነስ መሬትን በተደጋጋሚ አለማረስ፣ የአየር ንብረትን የሚቋቋሙ ሰብሎች ላይ ትኩረት ማድረግ፣ ብዙ ጊዜ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን ማስወገድ፣ ነጃጅ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን ደግሞ የኀይል አማራጭ በሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች መተካት፣ የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶችን ተመልሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ እና በከተሞች ያለውን የቆሻሻ አወጋገድ በተደራጀ መንገድ ማስወገድ እንደሚገባ እንደመፍትሔ ተቀምጠዋል።
የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ተስፋሁን አለምነህ እንዳሉት በዓለም ላይ ስጋት እየኾነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ስትራቴጂ ተግባራዊ ካደረገች ዓመታትን አስቆጥሯል። በክልሉ የሚገኙ ፋብሪካዎች ወደ አየር የሚለቀቁትንም ኾነ በፍሳሽ የሚያስወግዱትን ካርቦንዳይ ኦክሳይድ እና ኬሚካሎች (የሙቀት አማቂ ጋዝ) ልቀት ቆጠራ ባለመሠራቱ በክልሉ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ማወቅ ሳይቻል ቆይቷል ብለዋል። ይህ መኾኑ ደግሞ የሚታቀዱ የልማት ተግባራት ላይ እየደረሰ ያለው ውድመት መከላከል እና መቆጣጠር ሳይቻል መቆየቱም ተገልጿል።
ችግሩን ለመፍታትም ባለሥልጣኑ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በክልሉ ለሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት አስተዋጽኦ እያደረጉ ከሚገኙ ተቋማት ላይ ጥናት ማካሄዱን ገልጸዋል። ጥናቱ ፖሊሲ ለመንደፍ፣ ውሳኔ ለመስጠት በግብዓትነት ያገለግላል።
የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ቆጠራ ማለት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን ካርቦንዳይ ኦክሳይድ እና ሌሎች አማቂ ኬሚካሎች መጠን የሚለካበት መንገድ ነው።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!