
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አራተኛ ቀኑን በያዘው የመንግሥት ሠራተኞች ሥልጠና ወሳኝ የኾኑ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች እየተዳሰሱ ነው፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የአሥተዳደር ዘርፍ ተቋማት ሠልጣኖች ሥልጠናው ተቀራራቢ የአመለካከት እና የተግባር አንድነት ያመጣል ብለዋል፡፡
ሥልጠናው የፖለቲካ ስብራቶች የፈጠሩትን የአመለካከት እና የተግባር ልዩነት ለማቀራረብ ይረዳል ያሉት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት ኀላፊ መዓዛ በዛብህ የሰላም ባሕል ግንባታ የሥልጠናው ማዕከል ነበር ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር ያለንን ሃብት ማወቅ፣ ማሥተዳደር፣ መምራት እና መጠቀም ይኖርብናል ያሉት ኀላፊዋ የተዛባ ትርክትን ማረም እና ገዥ ትርክትን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ሥልጡን የመንግሥት ሠራተኞችን መገንባት የሚያስችል የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን እና የሁሉም ነገር መሠረት የኾነውን ሰላም በጋራ ለማጽናት ሁሉም የድርሻውን ይወስዳል ብለዋል፡፡
የምንገኝበት የመረጃ ዘመን ለተዛባ አረዳድ እና ለተሳሳተ ትርክት ስርጭት የጎላ አስተዋጽኦ ነበረው ያሉት የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ ችግሩ ሥር ሰድዶ አሁን ላለንበት የሰላም እጦት ምክንያት ኾኗል ብለዋል፡፡
መንግሥት ሠራተኛው ሰላምን በማስፈን ሂደት ውስጥ ሁለት ኀላፊነት አለበት ያሉት አቶ ደጀኔ ምክንያታዊ የመረጃ አጠቃቀም ሥርዓትን ማስፈን እና የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በመለየት እና በመፍታት ሥልጠናው የተግባር እና የአመለካከት መቀራረብ አምጥቷል ብለዋል፡፡
የመንግሥት ሠራተኛው የሕዝብ ቅሬታን የሚፈጥሩ ችግሮችን በማረም በኩል ሚናው የጎላ ነው ያሉት ደግሞ የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ባለሙያ አቶ ገበየሁ ጣሴ ናቸው፡፡
ሥልጠናው የአስተሳሰብ አንድነትን በመፍጠር በኩል ሥኬታማ ነበር ያሉት ሠልጣኙ የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል ሰላማዊ የትግል ሥርዓትን ያሳየ ጭምር ነበር ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!