
ጎንደር: ታኅሳሥ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ መልዕክት 5ኛው ዙር ሥልጠና በጎንደር ከተማ አሥተዳደር እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ለሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች እየተሰጠ ነው። ሃብትና ጸጋን በመጠቀም ሀገርን ማሳደግ እና ሀገራዊ ገዥ ትርክትን መፍጠር አንደሚገባ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈንታሁን ስጦታው ገልጸዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች የሰላምን አስፈላጊነትን ተረድተው ለሰላም እንዲሠሩ ማድረግ የዚህ ሥልጠና ዋና ዓላማ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡ አቶ ፈንታሁን በሥልጠናው ሀገራዊ አንድነትን በማናከር ሁሉም ለሀገር ግንባታ ኀላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ካሣሁን ንጉሴ በሥልጠናው ኅብረ ብሔራዊነት፣ አርበኝነት እና አንድነት ትኩረት እንደሚደረግባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ተሳታፊ የመንግሥት ሠራተኞች እንዳሉት ሥልጠናው ለአቅም ግንባታ እና የሕዝብ አገልጋይነት ሥሜትን ከፍ ለማድረግ እገዛ የሚያደርግ ነው።
ማኅበረሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል ሥልጠና መኾኑንም ሠልጣኝ የመንግሥት ሠራተኞቹ ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት መምሪያ ኀላፊ ፋሲል አብዩ ሥልጠናው የመንግሥት ሠራተኞች ለማኅበረሰቡ ታማኝ እና ቅን አገልጋይ እንዲኾኑ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ደስታ ካሣ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!