
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአስተሳሰብ አንድነት በማምጣት ሥራዎችን የሚመራና ለውጡን በተሻለ አስተሳሰብ በመምራት ለማስቀጠል ለመንግሥት ሠራተኛው ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
በአማራ ክልል የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የእቅድና በጀት ዳይሬክተር በሪሁን ተረፈ በሥልጠናው እየተሳተፉ እንደኾነ ለአሚኮ ተናግረዋል።
የሚሰጠው ሥልጠና በሚሠሩበት ተቋም ያለውን ሀብት አቀናጅተው በተገቢው መንገድ በመጠቀም ችግሮችን መፍታት እንደሚያስችላቸውም ነው የገለጹት።
”ከሥልጠና ስንመለስም ባደገ አስተሳሰብ፣ በአመለካከት አንድነት እና በቁርጠኝነት ሠርተን ውጤታማ እንኾናለን ብየ አስባለሁ” ብለዋል።
የሥልጠናው አስተባባሪ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቀለሙ ሙሉነህ የሚሰጠው ሥልጠና 5ኛ ዙር መኾኑን ገልጸዋል።
ከሥልጠናው በኋላ የተዳከመውን የአገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል የችግሮች መፍቻ አንድ መንገድ ኾኖ የሚወሰድ እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡
የአገልጋይነት ስሜትን፣ መነሳሳትን እና ውጤታማነትን እንደሚፈጠርም ነው አቶ ቀለሙ የገለጹት።
እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሥልጠና ወሳኝ መኾኑን ያመላከቱት አቶ ቀለሙ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አሥተዳደር ክፍተቶች በሥልጠናው ይሞላሉ ነው ያሉት።
ኅብረተሰቡን አዳምጦ ችግሮችን መፍታትም የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ በመኾኑ ሥልጠናው እየተሰጠ መኾኑን ገልጸዋል።
አቶ ቀለሙ ”የሕዝብ ጥያቄን ሊመልስ የሚችል ምሁርን ነው እያሰለጠንን ያለነው” ያሉት አቶ ቀለሙ ”የሕዝብን ጥያቄ የሚያዳምጥ እና የሚመልስ አመራር ለመፍጠር ነው እየሠራን ያለነው” ብለዋል። ሕዝቡም ከአመራሩ ጎን ኾኖ የአካባቢውን ልማት እንዲያፋጥን አሳስበዋል።
ሃብት ፈጠራና ማስተዳደር፣ ገዢ ትርክት ማዳበር እና ብሔራዊ አርበኝነት፣ የሲቪል ሰርቪስ እሳቤዎች እና አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም የሰላም ባሕል ግንባታ የሥልጠናው ይዘቶች መኾናቸው ተገልጿል።
የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለሥልጣን እና የጋፋት ኢንዶውመንት ሠራተኛ አባላት በሥልጠናው እየተሳተፉ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!