“ሥልጠናው ከነጠላ እና ከሀሰት ትርክቶች ወጥተን የጋራ ትርክትን ለመገንባት አስፈላጊ ነው” የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

33

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ሠራተኞች እና ምሁራን “ከእዳ ወደ ምንዳ” በሚል ርዕስ ሥልጠና እየወሰዱ ነው። ሥልጠናው አራት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መሰረት ተደርጎ እንደሚሰጥም ተገልጿል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት እና የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ሠራተኞች በሚሳተፉበት መድረክ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ “ሥልጠናው ከነጠላ እና ከሀሰት ትርክቶች ወጥተን የጋራ ትርክትን ለመገንባት አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ፋንቱ ሥልጠናው ኢትዮጵያ ከገባችበት ችግር ወጥታ እዳዋን ወደ ምንዳ የምትቀይርበት መንገድ መኾኑንም አስገንዝበዋል። ይህን ለመፈጸም አመራሮች አቅማቸውን አጎልብተው ቀዳሚ ተሰላፊ እና የችግሩ መፍቻ ቁልፍ እንዲኾኑ ለማድረግ መታቀዱንም ጠቁመዋል።ይህ ሥልጠና የመንግሥት ሠራተኞችን የማስፈጸም አቅም በማጎልበት የሀገር ግንባታውን ሥራ በጋራ ለመፈጸም አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማስረጽ ቀጣይ ትውልድ ለመገንባትም ምቹ ኹኔታ እንደሚፈጥርም ወይዘሮ ፋንቱ አንስተዋል። የተሸረሸረውን የአገልጋይነት ሥሜት ወደ ነበረበት በመመለስ ሥልጡን የመንግሥት ሠራተኞችን ለማፍራትም የሚያስችል ሥልጠና ስለመኾኑም አፈ ጉባኤዋ አንስተዋል።

የመሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ በበኩላቸው ሥልጠናው የመንግሥት ሠራተኞችን አቅም ለማጎልበት እና የሚፈጠሩ የመልካም አሥተዳዳር ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ብለዋል፡፡

ሠራተኛው ሥልጡን እና አገልጋይ እንዲኾን ለማድረግም ያስችላል ብለዋል፡፡ የአገልጋይነት ሥሜት ለመፍጠር እና ነፃ አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲያስችልም ይረዳል ነው ያሉት፡፡ አቶ ሲሳይ “ከነጠላ እና ከሀሰት ትርክቶች ወጥተን የጋራ ትርክትን ለመገንባት ሥልጠና አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእንግሊዛዊው ቢሊየነር ሰር ጂም ራትክሊፍ የማንቸስተር ዩናይትድን 25 በመቶ ድርሻ በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት መስማማታቸው ተነገረ።
Next article”የሚሰጠው ሥልጠና የሕዝብ ጥያቄን የሚመልስ አመራር ለመፍጠር ነው” የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ