
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ”ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ መልእክት በደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ብልፅግና ፓርቲ አባላት የመምሪያ እና የክፍለ ከተማ የመንግሥት ሠራተኞችና የምሁራን አባላት የ5ኛ ዙር ሥልጠና በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።
የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ደበበ አክሎግ አባላቱ በአመለካከት ተመሳሳይ ደረጃ እንዲደርስ ያለመ፣ ያሉበትን ብዥታዎች የሚያጠራ፣ አዳዲስ ዕሳቢዎችና አንድነትን የሚያመጣ ሥልጠና መኾኑን ገልጸዋል።
አባሉ አቅሙን እንዲያጎለብት፣ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለማረም፣ መልካም ስብዕናን ለመላበስ እንዲያስችል፣ ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ለማፅናት፣ የጋራና የወል ገዥ ትርክትን እንደ ሀገር ለመገንባት፣ ሥልጡንና አገልጋይ ሲቪል ሰርቫንት ለመገንባት፣ የሀብት አጠቃቀምና የአስተዉሎት ክህሎትን ለማሳደግ ሥልጠናው ትልቅ አቅም የሚፈጥር እንደኾነም አቶ ደበበ አክለው የገለፁት።
ሥልጠናው በሀብት መፍጠርና ማሥተዳደር ብልፅግናን ማረጋገጥ፣ የገዥ ትርክት ግንባታ፣ ሥልጡን ሲቪል ሰርቪስ መገንባት፣ የሰላም ባሕልና አመለካከት የመገንባትና የመምረጥ ክህሎት ላይ በማተኮር ከታህሳስ 15-18 ዓ.ም ለተከታታይ 4 ቀናት እንደሚሰጥ አቶ ደበበ ጨምረው ገልጸዋል።
የደብረታቦር ከተማ ከንቲባ ደሴ መኮንን ሥልጠናው ቆራጥ ሕዝብን በቀናነት ማገልገል የሚችል አባላት መፍጠር ዓላማ ያደረገ ነዉ ብለዋል።
ከንቲባው ያሉንን እምቅ የተፈጥሮ ፀጋዎችን እንዴት ወደ ሃብት መቀየር እንደምንችልና እንደ ሀገር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ከግብ ለማድረስ ሥልጠናው ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል፤ ሁሉም ሠልጣኝ ከሥልጠናው በሚያገኘው ዕውቀት በተሰማራበት የሥራ መስክ የተሻለ ውጤት ለማምጣት መትጋት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሠልጣኙ ለክልላችንና ለከተማችን ሰላም መሥራት እንደሚገባም ከንቲባው አስገንዝበዋል። ክልሉ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ እንዲሳካ ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!