
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ በስሜን ጎንድር በየዳ፣ ጃናሞራ እና ጠለምት እንዲኹም በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሰቆጣ፣ ፃግብጂ እና አበርገሌ ወረዳዎች በድርቅ ለተጎዱ የኀብረተሰብ ክፍሎች የሚውል 11ሺህ ኩንታል የበቆሎ ዱቄት ድጋፍ መደረጉን የአመልድ- ኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር ሺብሬ ጆርጋ (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡
ምክትል ዳይሬክተሯ እንዳሉት ፀደይ ባንክ፣ ዓባይ ባንክ እና በላይነህ ክንዴ ፋውንዴሽን በጠቅላላው 70 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ አመልድ- ኢትዮጵያ ድጋፉን እያስተባበረ በተገኘው ገንዘብ ጥራቱን የጠበቀ 11ሺህ ኩንታል የበቆሎ ዱቄት ተገዝቶ 80 ሺህ ለሚኾኑ በድርቁ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች ለማድረስ በማጓጓዝ ላይ ነው ብለዋል፡፡
የፀደይ ባንክ ፕሬዚዳንት መኮንን የለውምወሰን “በክልሉ በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ምክንያት ለችግር የተዳረጉትን ወገኖች ሕይወት ለመታደግ አመልድ -ኢትዮጵያ የዕለት ደራሽ ምግብ ገዝቶ እንዲያቀርብ 50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገናል” ብለዋል፡፡አቶ መኮንን ሌሎች ባንኮች እና ኢንሹራንሶችም የእነሱን አርዓያ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!