በተፋሰስ ልማት 16 ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረጉን የጋዝጊብላ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

15

ሰቆጣ: ታኅሳስ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጋዝጊብላ ወረዳ 21 ቀበሌዎች ያሏት ሲኾን 72 የደን ተፋሰሶች በወረዳው ውስጥ ይገኛሉ።

ወጣት ሻንበል ገላው የአስ ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪ ነው። በ01 ቀበሌ ባለው ተፋሰስ ከሌሎች 40 ወጣቶች ጋር በመደራጀት 23 ሺህ በላይ ዛፎችን በመትከል እና በማልማት ተጠቃሚ እንደኾኑ ነግሮናል።

“ከ2013 ዓ.ም ጀምረን በተከልናቸው ዛፎች እንደማኅበር ተጠቃሚ ኾነናል” ብሏል። ወጣቶቹ በንብ እርባታ፣ በእንሰሳት ማድለብ፣ በአረንጓዴ ልማት እና በአትክልት እና ፍራፍሬ ተጠቃሚ እንደኾኑ ተናግረዋል።

ወጣቱ ጥበቃ ቀጥረው በአረንጓዴ አሻራ ልማት ተጠቃሚ ከመኾናቸው ባለፈ የአካባቢውን የተራቆተ ቦታም መቀየር እንደቻሉ አስገንዝበዋል።

የወረዳው ደን ልማት ባለሙያ አቶ ግርማ በርወይ ከሬድ መንግሥታዊ ያልኾነ ድርጅት ጋር በመተባበር ለወጣቶች የሥልጠና እና የግብዓት ድጋፍ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
ለቀጣይም ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ተፋሰሱ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ እንዲኾን እንደሚሠሩም አብራርተዋል።

በወረዳው ከሚገኙ ከ72 ተፋሰሶች ውስጥ በ44 ተፋሰሶች በተሠራው የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ የአፈር መሸርሸርን ከመከላከል ባለፈ በአረንጓዴ ልማት ሥራ 16 ሺህ 768 ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረጉን የጋዝጊብላ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ ንጋቱ አስረሳው ገልጸዋል።

ለወጣቶቹ ሥልጠና በመስጠት በንብ እርባታ፣ በእንሰሳት ማድለብ፣ በአረንጓዴ ልማት እና በአትክልት እና ፍራፍሬ ተጠቃሚ ማድረግ ችለናል ብለዋል።

ለቀጣይም በጦርነቱ ምክንያት ተዳክመው የነበሩ ተፋሰሶችን ወደ ቀደመ አቅማቸው በመመለስ 724 ወጣቶችን የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠሩ እንደሚገኙም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”ልማታችን እንዳይስተጓጎል ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ እንፍታ” የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ
Next article“እየተካሄዱ ያሉ ሥልጠናዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እና የአመራሩን አቅም ለመገንባት እድል ይሰጣሉ” የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር