
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ተፈሪ ታረቀኝ ገልጸዋል።
የክልሉ ኢንዱስትሪዎች ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ ለ28 ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን እና ወደ ዉጪ ከተላከ ምርትም 138 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ነው አቶ ተፈሪ የተናገሩት።
በ2016 በጀት ዓመትም የበለጠ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የጠቀሱት አቶ ተፈሪ የተከሰተው የሰላም ችግር ግን እንቅፋት እየኾነ ነው ብለዋል።
ግጭቱ እንደ ጣና ፍሎራ ባሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ መኾኑን ነው ምክትል ቢሮ ኀላፊው የገለጹት።
አቶ ተፈሪ ኢንዱስትሪዎች ከደረሰባቸው ጉዳት አገግመው ሥራ ለማስጀመር የክልሉ መንግሥት አጥንቶ ከባለሃብቶቹ ጋር ውይይት ማድረጉን ጠቁመዋል። ”ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና ልማታችን እንዳይስተጓጎል ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ እንፍታ” ሲሉም አሳስበዋል።
ሌሎች አምራቾችም ግብዓት ለማግኘት፣ ለማምረት እና ምርታቸውን ለገበያ ለማድረስ መቸገራቸውን ገልጸዋል። የኢንዱስትሪዎቹ ተቀጣሪ የነበሩ ሠራተኞችም ለሥራ አጥነት መዳረጋቸውን ጠቅሰዋል።
የሰላም ችግሩ ጫና ካደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎች ውስጥ አንዱ ዩኒሰን የምግብ ዘይት ፋብሪካ ነው። ፋብሪካው በቀን 33 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት የማምረት አቅም ቢኖረውም ግብዓት ለማግኘትም ኾነ ምርቱን ለማከፋፈል እንደልብ መንቀሳቀስ አለመቻሉን የዩኒሰን ኮርፖሬት ግሩፕ የኮሚኒኬሽን ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ማናጀር ኃይለእየሱስ ፍላቴ ገልጸዋል።
ተረፈ ምርቶችንም አዲስ አበባ እና ናዝሬት ለሚገኙ ፋብሪካዎች ለማድረስ መቸገራቸውንም ነው የተናገሩት። አቶ ኃይለእየሱስ ለሕዝብ እና ለሀገር ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ሰላም እንዲፈጠር ችግሮችን በውይይት መፍታት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!