በጥጥ ምርት ላይ እየታየ ያለው የገብያ ትስስር ችግር እንዲቀረፍላቸው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አልሚ ባለሃብቶች ጠየቁ።

67

ሁመራ: ታኅሳስ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በ2015/16 የምርት ዘመን ከ550 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች የለማ ሲኾን ከዚህም ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

በዞኑ በቃብትያ ሁመራ ወረዳ በበዓከር ቀበሌ አካባቢ በጥጥ ምርት ላይ ተሠማርተው ያገኘናቸው አልሚ ባለሃብቶች የጥጥ ሰብል የሚሰበሰብበት ወቅት በመኾኑ የጉልበት ሠራተኞችን በመጠቀም ሰብላቸውን እየሠበሠቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

150 ሄክታር መሬት ላይ የጥጥ ሰብል አልምተው ምርታቸውን እየሠበሠቡ እንደሚገኙ የተናገሩት አልሚ ባለሃብት አቶ ስዩም ዳኘው ከ100 በላይ የጉልበት ሠራተኞችን በመጠቀም የጥጥ ምርትን እያስለቀሙ መኾኑን ነግረውናል።

ሌላኛው አልሚ ባለሃብት አቶ ተስፋየ እርጥቤ በ100 ሄክታር መሬት ላይ የጥጥ ምርትን በማልማት ውጤታማ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በ2015 የምርት ዘመን የጥጥ ሰብል በስፋት ማልማታቸውን እና በአካባቢያቸው የብድር አገልግሎት ባለመኖሩ በባለፈው ዓመት ከፍተኛ ወጭ አውጥተው ያመረቱት ምርት የገብያ ትስስር ችግር በመፈጠሩ ኪሳራ እንዳጋጠማቸው አስታውሰዋል።

በዘንድሮው የምርት ዘመን ከራሳቸው አልፎ ለሀገር ምጣኔ ሃብት ጠቀሜታ ያለው ምርት ማምረታቸውን የገለጹት አልሚዎቹ ያመረቱት ምርት የገብያ ችግር እንዳይገጥመው ሰጋት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
መንግሥት የገብያ ትስስር ችግርን እንዲቀርፍላቸውም ጠይቀዋል።

የቃብትያ ሁመራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሳሙኤል ሰለሞን በወረዳው በ2015/16 የምርት ዘመን ከ61 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በጥጥ ምርት ለማልማት ታቅዶ 6 ሺህ 247 ሄክታር መሬት በጥጥ ምርት መሸፈኑን ገልጸዋል።

በ2015 የምርት ዘመን የነበረው የገብያ ትስስር ችግር በ2016 የጥጥ ምርት በስፋት እንዳይለማ እንቅፋት መኾኑንም ጠቁመዋል።

በ2015/16 የምርት ዘመን በዞኑ ሰሊጥ እና ማሽላ በስፋት መልማቱን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ የኤክስቴንሽን ቡድን መሪ በሪሁን ፀጋየ ገልጸዋል።

በዞኑ 6 ሺህ 900 ሄክታር መሬት በጥጥ ሰብል መልማቱን አንስተው 69 ሺህ 400 ኩንታል የጥጥ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 3 ሺህ 600 ሄክታር የጥጥ ምርት መሠብሠቡን አንስተዋል። በጥጥ ምርት ላይ ያለውን የገብያ ችግር ለመቅረፍ ከዞኑ ንግድና ገቢያ ልማት መምሪያ ጋር በቅርበት እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በዞኑ በ2015/16 ከለማው 550 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 97 በመቶ የሚኾነው ሰብል መሠብሠቡን የገለጹት አቶ በሪሁን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከተሠበሠበው ሰብል ውስጥ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሠብሠብ ተችሏል ብለዋል።

ዘጋቢ- ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጠንካራ እና የታፈረች ሀገር ለመፍጠር በዕውቀት የበለጸገ ዜጋ ያስፈልጋል” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next articleበኩር ጋዜጣ ታኅሳስ 15/2016 ዓ.ም ዕትም