“ጠንካራ እና የታፈረች ሀገር ለመፍጠር በዕውቀት የበለጸገ ዜጋ ያስፈልጋል” አቶ ይርጋ ሲሳይ

18

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስደው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እና ያስፈተኗቸውን ሁሉንም ተማሪዎች ላሳለፉ ትምህርት ቤቶች የዕውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር አካሂዷል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በመድረኩ ላይ ተገኝተው የማጠቃለያ መልእክት አስተላልፈዋል። ጠንካራ እና የታፈረች ሀገር ለመፍጠር በዕውቀት የበለጸገ ዜጋ ያስፈልጋል ሲሉ አስገንዝበዋል። ለዚህም ሰላሙ የተረጋገጠ የመማር ማስተማር አካባቢ እና ጠንካራ የኾነ የትምህርት ሥርዓት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ጭምር ተጽእኖ አሳድሮ እንደቆየ ገልጸዋል። ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት ነው፤ ሰላም እንዲደፈርስ የሚጥሩ አካላትም ራሳቸው ያለሰላም ሊኖሩ እንደማይችሉ መገንዘብ አለባቸው ብለዋል አቶ ይርጋ።

ሰላም እንዲደፈርስ የሚጥሩ አካላት ተማሪዎች እንዳይማሩ እና ተወዳዳሪ ትውልድ እንዳይፈጠር እያደረጉ ነው ብለዋል። የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም መላ ሰላም ወዳድ ዜጎች ሰላም የሚያደፈርሱ አካላትን በውል ተረድተው “ተዉ” ማለት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ባልተገባ ተግባር ላይ የተሠማሩ አካላትም ለራሳቸው እና ለሕዝብ ሲሉ ወደሰላማዊ መንገድ በመመለስ በሚጠቀሙበት የሥራ መስክ ላይ መሠማራት እንዳለባቸው አቶ ይርጋ አስገንዝበዋል።

መንግሥት ለሰላም ባለው ጽኑ ፍላጎት መሠረት በልዩነት ለቆሙት አካላት በሙሉ የሰላም ጥሪ አድርጓል ብለዋል። የሰላም ጥሩዉ ክልሉ በዘላቂነት እንዲረጋጋ፣ ዜጎች ያለስጋት ሠርተው እንዲቀየሩ፣ ትምህርት ቤቶች ያለምንም ኮሽታ የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲያከናውኑ እንዲሁም በሁሉም መስክ ተወዳዳሪ ዜጋ እንዲፈጠር የሚያስችል ስለመኾኑም አብራርተዋል።

አቶ ይርጋ የዛሬ ተሸላሚ ተማሪዎች ችግር ሳያሸንፋቸው፣ ይልቁንም የተፈጠረውን ችግር በበላይነት አሸንፈው ለውጤት የበቁ መኾናቸውን አመላክተዋል። ለአማራ ክልል ብሎም ለኢትዮጵያ እንዲህ አይነት በርካታ ብርቱ ልጆች እንደሚያስፈልጓትም አንስተዋል።

ተሸላሚ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውም ይህንኑ ውጤት በመድገም ሕዝብን እና ሀገርን የሚጠቅም ዕውቀት እና ክህሎት ይዘው እንዲወጡ አቶ ይርጋ አሳስበዋል። የእንኳን ደሥ ያላችሁ መልእክትም ለተማሪዎች አድርሰዋል።

በክልሉ የሚገኙ ተማሪዎች የበለጠ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ እና ሀገርን በወጉ እንዲረከቡ ትምህርት ቤቶች በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የክልሉ ሰላም ሙሉ በሙሉ ተረጋግጦ በሁሉም አካባቢ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ተቀብለው እንዲያስተምሩ የክልሉ መንግሥት ከሕዝቡ ጋር በመኾን እየሠራ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ተምረን ጥሩ ውጤት ማምጣት፣ ተወዳድረን ማሸነፍ እንጅ እየተተኮሰብን ወደኋላ መቅረትን አንሻም” ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች
Next articleበጥጥ ምርት ላይ እየታየ ያለው የገብያ ትስስር ችግር እንዲቀረፍላቸው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አልሚ ባለሃብቶች ጠየቁ።